አዲስ ስፔስ ፎረም 2019
አዲስ ስፔስ ፎረም 2019

አምባሳደሮች፣ የሕዋ ኤጀንሲ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ተመራማሪዎች የተሳተፉበት 2ኛው የአዲስ ሕዋ ፎረም ትናንት በአዲስ አበባ በይፋ ተጀምሯል። ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ የአፍሪቃ ስፔስ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት እና የናይጄሪያ ኤምባሲ በጋራ ያዘጋጁት ይህ መድረክ፣ አፍሪቃ በዓለም አቀፉ የሕዋ ዘርፍ ተገልጋይ ብቻ ከመሆን አልፋ ፈጣሪ፣ አስተዋጽኦ አበርካችና ውሳኔ ሰጪ የምትሆንበትን መንገድ ለመቀየስ ያለመ ነው።

ፎረሙ ፖሊሲን፣ ቴክኒካዊ አቅምንና ዓለም አቀፍ ትብብርን በማስተሳሰር አህጉሪቱን ከሕዋ ዲፕሎማሲ ወደ እውነተኛ የሕዋ መሪነት ማሸጋገር ላይ ትኩረት አድርጓል።

የኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የሕዋ አቅምና የአገር ውስጥ ሳተላይት ግንባታ

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ይሹሩን ዓለማየሁ፣ እውነተኛ የሕዋ መሪነት በጠንካራ ፖሊሲ በተደገፈ ተጨባጭ ቴክኒካዊ አቅም እንደሚጀምር ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ የሳተላይት መረጃዎችንና የሕዋ አየር ንብረት ክትትልን ለግብርና፣ ለከተማ ፕላን፣ ለአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ ለተፈጥሮ ሀብት አስተዳደርና ለብሔራዊ ደኅንነት በማዋል ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ይሹሩን ዓለማየሁ
የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ይሹሩን ዓለማየሁ

ዶ/ር ይሽሩን የኢትዮጵያን ቀጣይ የሕዋ ጉዞ የሚያመላክቱ ዋና ዋና እርምጃዎችንም ይፋ አድርገዋል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካመጠቀቻቸው ሁለት የምድር ምልከታ ሳተላይቶች ልምድ በመነሳት፣ በአሁኑ ወቅት ሦስተኛ የምድር ምልከታ ሳተላይትና የመገናኛ ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል። ሁለቱም ተልዕኮዎች የዩኤን ኮፑዎስ የሕዋ ብክለት መከላከያ መመሪያዎችን ባከበረ መልኩ የሚከናወኑ ናቸው። በተጨማሪም የሕዋ-አየር ንብረት መረጃ መቀበያና መተንተኛ መሠረተ ልማት እየተገነባ ሲሆን፣ በምሥራቅ አፍሪቃ ለአገር ውስጥ የሳተላይት ዲዛይን፣ ምርት፣ ግንባታና ፍተሻ መሠረት የሚጥል ልዩ ክፍል እየተቋቋመ መሆኑን አስታውቀዋል። ዲፕሎማቶችና የምርምር ተቋማት በጋራ ምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ከስ.ሳ.ጂ.ኢ ጋር በቅርበት እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።

Advertisement

አዲስ አበባ የአፍሪቃ የሕዋ ዲፕሎማሲ መዲና

የአፍሪቃ ስፔስ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት መስራች የሆኑት ኤቲም ኦፊዮንግ፣ የአፍሪቃ አህጉራዊ የሕዋ አስተዳደር እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ ያለፈበትን ጉዞ በማስታወስ፣ እ.ኤ.አ የ2016ቱ የአፍሪቃ የሕዋ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም የአፍሪቃን ስፔስ ኤጀንሲ መመስረት ታሪካዊ ምዕራፎች መሆናቸውን ገልጸዋል። እ.ኤ.አ በ2022 የተመሰረተው አስሊ የብሔራዊ የሕዋ ኤጀንሲዎችን የምህንድስና ሥራ ለማገዝ በሕዋ ፖሊሲ፣ ሕግ፣ አስተዳደርና አመራር ላይ እንደሚያተኩር አብራርተዋል።

የአፍሪቃ ስፔስ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት መስራች ኤቲም ኦፊዮንግ
የአፍሪቃ ስፔስ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት መስራች ኤቲም ኦፊዮንግ
Cosmic Cliffs Magic Mug
Cosmic Cliffs Magic Mug
Get Yours

አዲስ አበባ የአፍሪቃን ኅብረት ፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪቃ ኢኪኖሚ ኮሚሽን እና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ቀጠናዊ ጽሕፈት ቤቶች መቀመጫ በመሆኗ የአፍሪቃ የሕዋ ዲፕሎማሲ ተፈጥሯዊ ማዕከል እንደሆነች ተናግረዋል። የሕዋ ዘርፍ ከፍተኛ ወጪና ስጋት ያለበት በመሆኑ አገራት በብቸኝነት ሊወጡት እንደማይችሉ ጠቅሰው፣ በሬዲዮ ሞገድ ክፍፍልና በምህዋር ድልድል ላይ የሚተላለፉ ዓለም አቀፍ ውሳኔዎች አስገዳጅ ስለሆኑ አፍሪቃ አስቀድማ በጋራ መዘጋጀት እንዳለባት አሳስበዋል።

የአፍሪቃ የሕዋ ኢኮኖሚ እድገትና የመበታተን ፈተና

በተባበሩት መንግስታት የአፍሪቃ ኢኪኖሚ ኮሚሽን የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አንድሬ ኖንጊየርማ በበኩላቸው፣ የዛሬው ዋና ጥያቄ አፍሪቃ ወደ ሕዋ ትሂድ ወይስ አትሂድ የሚለው ሳይሆን አፍሪቃውያን በጋራ መጓዝ ይችላሉ ወይ የሚለው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። እስካሁን ወደ 70 የሚጠጉ የአፍሪቃ ሳተላይቶች ወደ ምህዋር መምጠቃቸውንና ከ30 በላይ የሚሆኑት በሥራ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በአህጉሪቱ ከ20 በላይ ብሔራዊ የሕዋ ኤጀንሲዎችና ከ350 በላይ ተቋማት እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል። የአፍሪቃ የሕዋ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት ወደ 25 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን፣ በ2030 ከ50 ቢሊዮን ዶላር እንደሚበልጥ ይጠበቃል።

የአፍሪቃ ኢኪኖሚ ኮሚሽን የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አንድሬ ኖንጊየርማ
የአፍሪቃ ኢኪኖሚ ኮሚሽን የጂኦስፓሻል መረጃ አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አንድሬ ኖንጊየርማ
Related ESSS Launches Youth Wing and Forges Strategic Space Medicine Partnership with iTena

ሆኖም በ2026 ብቻ በተለያዩ የአፍሪቃ አገራት በርካታ የሕዋ ጉባኤዎች መካሄዳቸውን በማንሳት፣ ይህ እንቅስቃሴ ዘርፉ ሕያው መሆኑንና ወጣቶች በጉጉት እየተሳተፉ መሆኑን የሚያሳይ መልካም ምልክት ቢሆንም፣ ያለ ቅንጅት ከቀጠለ ወደ መበታተንና ሀብት ብክነት ሊያመራ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። አፍሪቃ 55 የተነጣጠሉ የሕዋ ዕቅዶች ሳይሆን በአንድ አህጉራዊ ራዕይ የተሳሰሩ ብሔራዊ ፕሮግራሞች እንደሚያስፈልጓት ገልጸው፣ የዘርፉ ስኬት መለካት ያለበት በመጠቁ ሳተላይቶች ቁጥር ሳይሆን በምድር ላይ በተሻሻለው የአርሶ አደሮችና የዜጎች ሕይወት መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

እ.ኤ.አ ለ2027 ወሳኝ ዓለም አቀፍ መድረኮች በአንድ ድምፅ መዘጋጀት

የአፍሪቃን ስፔስ ካውንስል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቲዲያኔ ዋታራን በመወከል ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ታንዲኪሌ ቺሳላ ምብቩንዱላ፣ በ2027 ለሚካሄዱ ሦስት ወሳኝ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች አፍሪቃ የተቀናጀ አቋም መያዝ እንዳለባት አሳስበዋል። እነዚህም በሻንጋይ የሚካሄደው ወርልድ ሬዲዮኮሙኒኬሽን ኮንፈረንስ፣ በአዲስ አበባ የሚስተናገደው ኮፕ 32 እና 60ኛውን የውጭ ሕዋ ስምምነት ዓመት የሚያከብረው የዩኤን ኮፑዎስ ጉባኤ ናቸው።

የአፍሪቃን ስፔስ ካውንስል  ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ታንዲኪሌ ቺሳላ ምብቩንዱላ
የአፍሪቃን ስፔስ ካውንስል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ታንዲኪሌ ቺሳላ ምብቩንዱላ

በሚያዝያ 2025 በካይሮ በይፋ ሥራ የጀመረው የአፍሪቃ ስፔስ ኤጀንሲ፣ የ55ቱን ሀገራት ብሔራዊ የሕዋ ኤጀንሲዎችን ሥራ ለመድገም ሳይሆን ለማስተባበር የተቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል። ኤጀንሲው የራሳቸው የሕዋ ኤጀንሲ የሌላቸውን ጨምሮ ሁሉንም 55 የአፍሪቃ ኅብረት አባል አገራት የማገልገል ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅትም በ45 አገራት ከ20 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን ተደራሽ ባደረገው ጂኤምኢኤስ አፍሪቃ ፕሮግራምና በ100 ሚሊዮን ዩሮ በሚደገፈው አፍሪቃ-ኢዩ ስፔስ አጋርነት ፕሮግራም በኩል ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አስረድተዋል። በ2026 ብቻ 30 አፍሪቃውያን ባለሙያዎች ከፍተኛ የቴክኒክ ሥልጠና ያገኙ ሲሆን፣ 40 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። ሕዋን የሚረዱ ዲፕሎማቶችንና ዲፕሎማሲን የሚረዱ የሕዋ ባለሙያዎችን ማፍራት ለአህጉሪቱ ስኬት ወሳኝ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

Advertisement
Hewa+ Ad
Ad

የ50 ቢሊዮን ዶላር የፈንድ ጥሪና የሰው ኃይል ልማት

የመክፈቻ ንግግሩን ያጠቃለሉት በኢትዮጵያ የናይጄሪያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ክቡር ኤች. አሊ-ጎቤ፣ አፍሪቃ ከጥንት ጀምሮ ከሰማያትና ከሥነ ፈለክ ዕውቀት ጋር ጥልቅ ታሪካዊ ቁርኝት እንዳላት በማስታወስ፣ ይህንን ቅርስ ወደ ዘመናዊ የሳይንስና የኢንዱስትሪ አቅም የመቀየር ኃላፊነት እንዳለባት ገልጸዋል። የሕዋ ቴክኖሎጂ ወደ ጨረቃ ወይም ማርስ መጓዝ ብቻ ሳይሆን በምድር ላይ ያሉ የምግብ ዋስትናና የልማት ችግሮችን የሚፈታ ተግባራዊ መሣሪያ መሆኑን አስረድተዋል።

የናይጄሪያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ክቡር ኤች. አሊ-ጎቤ
የናይጄሪያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ክቡር ኤች. አሊ-ጎቤ
Planets Pack (10-Piece Sticker Set)
Planets Pack (10-Piece Sticker Set)
Get Yours

በናይጄሪያ በተመሳሳይ ጊዜ እየተካሄደ ባለው የአፍሪቃ የሕዋ ኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ የቀድሞው የአፍሪቃን ዴቨሎፕመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር አኪንዉሚ አዴሲና በ5 ቢሊዮን ዶላር መነሻ ካፒታል የሚቋቋም የ50 ቢሊዮን ዶላር የአፍሪቃ የሕዋ ወደፊት ፈንድ እንዲመሰረት ያቀረቡትን ሐሳብ በማንሳት፣ የዘርፉን ግዙፍ የፋይናንስ ፍላጎት አመላክተዋል። እንዲሁም ፓን-አፍሪቃን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ስፔስ ሳይንስ እንዲቋቋም ድጋፋቸውን ገልጸው፣ በ2027 የሚካሄደው 3ኛው የአዲስ ሕዋ ፎረም ኢትዮጵያ ከምታስተናግደው ኮፕ 32 ጋር እንዲቀናጅ ጠይቀዋል።

ከውይይት ወደ ተግባራዊ ቅንጅት

በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል እየተካሄደ የሚገኘው 2ኛው የአዲስ ሕዋ ፎረም ዛሬ ዓርብ ኅዳር 18 ቀን 2019 ዓ.ም. ይቀጥላል። በቀሪዎቹ መርሐ ግብሮችም ቴክኒካዊ የሕዋ ማብራሪያዎች፣ የሁለትዮሽና የርዕሰ ጉዳይ የክብ ጠረጴዛ ውይይቶች እንዲሁም የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና ምርምር ማዕከል ጉብኝት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።