በድቅድቅ ጨለማ፣ ከከተማው ጫጫታ እና ሰው ሰራሽ ብርሃን ርቀው ወደ ሰማይ ቀና ብለው ያውቃሉ? ጥርት ባለ ማታ፣ በገጠር ወይም በከፍተኛ ተራራ ላይ ሆነው ከላይ የተነጠፈውን ማለቂያ የሌለውን የከዋክብት ስብስብ ሲመለከቱ፣ አንድ ጥልቅ የሆነና ቃላት ሊገልጹት የማይችሉት ስሜት ውስጥ መግባትዎ አይቀርም። የሰው ልጅ የድንጋይ መሳሪያዎችን መከርከም ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ዛሬ እጅግ የረቀቁ ቴሌስኮፖችን ወደ ህዋ እስከላከበት ጊዜ ድረስ፣ ወደ ሰማይ እያየ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ደጋግሞ ይጠይቃል፦ "ከእኛ ውጪ ሌላ ማንም የለም ይሆን? በዕውኑ በዚህ ማለቂያ በሌለው ግዙፍ አጽናፈ ዓለም ውስጥ ብቻችንን ነን?"
ይህ ጥያቄ ከሳይንስም በላይ ነው። የሰው ልጅ የራሱን ማንነት፣ አመጣጥ እና በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያለውን ቦታ ለመረዳት የሚያደርገው ጥልቅ ፍለጋ ነው። እኛ በዚህች ሰማያዊ ነጠብጣብ በሆነች ትንሽ መሬት ላይ ሆነን፣ አእምሯችን ግን ከምድር ስበት አምልጦ ሚሊዮን የብርሃን ዓመታትን ሲያቋርጥ ማሰብ በራሱ አስገራሚ ነው። ዛሬ ዘመናዊው ሳይንስ ይህንን የዘመናት ጥያቄ በስሜት ብቻ ሳይሆን፣ በተጨባጭ ቁጥሮች፣ ስሌቶች እና ጥልቅ ምልከታዎች ለመመለስ እየጣረ ይገኛል።
ከአሸዋ ቅንጣት የሚበዙት የብርሃን ነጠብጣቦች
ስለ አጽናፈ ዓለማችን ግዙፍነት ስናወራ፣ አእምሯችን በቀላሉ ሊገነዘበው ከሚችለው ልኬት እጅግ የራቀ ነው። የቁጥሮቹን ግዝፈት ለመረዳት ከራሳችን ሰፈር እንጀምር። እኛ የምንኖርባት ፀሐይ እና ዙሪያዋን የሚሽከረከሩት ፈለኮች፣ ፍኖተ ሃሊብ በሚባለው እጅግ ግዙፍ ረጨት ውስጥ ይገኛሉ።
በዚህ የኛ ረጨት ውስጥ ብቻ፣ ከ100 ቢሊዮን እስከ 400 ቢሊዮን የሚገመቱ እንደ እኛ ፀሐይ የሚያበሩ ከዋክብት አሉ። በአንድ ሚሊዮን እና በአንድ ቢሊዮን መካከል ያለውን እጅግ ሰፊ የቁጥር ልዩነት በዓይነ ህሊናችን በግልጽ ለመሳል፣ ነገሩን በሰከንዶች አስበነው እንመልከት። አንድ ሚሊዮን ሰከንዶች ማለት ወደ አስራ አንድ ቀን ተኩል ገደማ ሲሆን አንድ ቢሊዮን ሰከንዶች ለማሳለፍ... ወደ ሰላሳ ሁለት ዓመታት ገደማ ይፈጃል! እንግዲህ የእኛ ረጨት ብቻ በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብትን አቅፋለች ስንል፣ በአንድ ረጨት ውስጥ ብቻ ያለው የከዋክብት ብዛት ምን ያህል ለማሰብ እንደሚከብድ መገመት ቀላል ነው።
ይሁን እንጂ ነገሩ በዚህ አያበቃም። እጅግ አቅርበው እና አጥርተው ማሳየት በሚችሉ የዘመናችን ቴሌስኮፖች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ከእኛ ፍኖተ ሃሊብ ውጪ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከ200 ቢሊዮን እስከ 2 ትሪሊዮን የሚደርሱ ሌሎች ረጨቶች አሉ። እያንዳንዳቸው እነዚህ ረጨቶች በውስጣቸው በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የራሳቸው ከዋክብት አሏቸው።
ይህንን መጠን በዓይነ ህሊናዎ ለመሳል እንዲህ ብለን እናስበው፦ በዓለማችን ላይ ወዳሉት በረሃዎች ፣ ውቅያኖሶች፣ ባህሮች እና ሀይቆች ዳርቻዎች በሙሉ እንሂድ። እዚያ የሚገኙትን እጅግ ጥቃቅን የአሸዋ ቅንጣቶች በሙሉ ብንቆጥር፣ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት የከዋክብት ብዛት በምድር ላይ ካሉት የአሸዋ ቅንጣቶች በሙሉ በአስር እጥፍ ይበልጣል!

በአጽናፈ ዓለማችን ውስጥ ያሉት ከዋክብት በምድራችን ላይ ላሉት ለእያንዳንዱ የአሸዋ ዘለላዎች በእኩል ቢካፈሉ፣ ለአንድ የአሸዋ ዘለላ እስከ 10,000 ከዋክብት ይደርሱታል!
የህይወት መፍለቂያ የሆኑት ምቹ ፈለኮች
ሳይንቲስቶች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደረጉ ተከታታይ ግኝቶች አንድ አስገራሚ እውነታ ላይ ደርሰዋል። ይኸውም በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካሉት ከዋክብት መካከል አብዛኛዎቹ ብቻቸውን አለመሆናቸውን ነው። እንደው ለስሌት ያህል፣ እያንዳንዱ ኮከብ ቢያንስ አንድ ፈለክ ብቻ አለው ብለን ብናስብ እንኳን፣ በአጽናፈ ዓለማችን ውስጥ ያሉት የፈለኮች ብዛት ከከዋክብቱ ጋር እኩል ወይም ከዚያም በላይ ነው ማለት ነው። ልክ እንደኛዋ ፀሐይ፣ ማለቂያ የሌላቸው ፈለኮች በየከዋክብቶቻቸው ዙሪያ ይሽከረከራሉ።
ከእነዚህ ማለቂያ ከሌላቸው ፈለኮች መካከል፣ ሁሉም ለህይወት ምቹ ናቸው ማለት አይደለም። አንዳንዶቹ ወደ ፀሐያቸው በጣም በመቅረባቸው የተነሳ ብረት እንኳን ሊያቀልጥ የሚችል ሙቀት አላቸው፤ ሌሎች ደግሞ እጅግ በመራቃቸው በረዷማ ናቸው። ነገር ግን፣ ትክክለኛው ርቀት ላይ የሚገኙ፣ ማለትም ውሃ በፈሳሽነት ሊኖርባቸው የሚችል ተመጣጣኝ ሙቀት ያላቸው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ፈለኮች አሉ። በእኛ ረጨት ውስጥ ብቻ ወደ 40 ቢሊዮን የሚጠጉ መሬትን የሚመስሉ፣ ምቹ ርቀት ላይ ያሉ ፈለኮች እንዳሉ ይገመታል። ቁጥሩ ይህን ያህል ግዙፍ ከሆነ፣ "ህይወት በምድር ላይ ብቻ የተገደበ ነው" ብሎ ማሰብ የሂሳብን ስሌት መካድ አይሆንም?
የሰው ልጅ የዕድገት ፍጥነት፡ ከድንጋይ ዋሻ እስከ ጠፈር መንኮራኩር
የሌሎች ስልጣኔዎችን መኖር እና አለመኖር በሚገባ ለመገምገም፣ የራሳችንን የሰው ልጅ የዕድገት ጉዞ ዞር ብሎ መመልከት እጅግ ወሳኝ ነው። የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ መኖር ከጀመረ ወደ 300 ሺህ ዓመታት ገደማ ሆኖታል። ለአብዛኛው የዚህ ጊዜ ክፍል፣ ማለትም ለመቶ ሺህዎች ዓመታት፣ አያቶቻችን በዋሻ ውስጥ እየኖሩ፣ አደን እያደኑ እና ቀላል የድንጋይ መሳሪያዎችን እየተጠቀሙ ነበር ጊዜያቸውን ያሳለፉት። የዕድገት ፍጥነቱ እጅግ አዝጋሚ ነበር።

የሰው ልጅ ስልጣኔ በግዜ ሂደት
ነገር ግን ከ10 ሺህ ዓመታት በፊት አካባቢ አንድ ትልቅ ለውጥ ተፈጠረ። የሰው ልጅ እርሻን አገኘ፣ መንደሮችን መሰረተ፣ እና አሁን የምናውቀውን የሰለጠነ ማህበረሰብ መገንባት ጀመረ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ያለው የ10 ሺህ ዓመታት ታሪክ የከተሞች፣ የቋንቋዎች እና የፈጠራዎች ታሪክ ነው።
ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ አሁን ያለንበት የመጨረሻው መቶ ዓመት ነው። በመቶ ዓመታት ውስጥ ብቻ ከፈረስ ጋሪ ወደ አውሮፕላን፣ ከሻማ ብርሃን ወደ ኤሌክትሪክ፣ ከደብዳቤ ልውውጥ ወደ ራዲዮ ሞገድ፣ እና በመጨረሻም የሰው ልጅን ከምድር አልፎ ጨረቃ ላይ እስከማሳረፍ ደርሰናል። ዛሬ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና እጅግ የረቀቁ የኮምፒውተር ስሌቶች ዓለማችንን በሰከንዶች ውስጥ እየቀየሯት ነው።
አስፈሪው ጸጥታ፡ ታዲያ ሌሎቹ የት አሉ?
የአጽናፈ ዓለማችን ዕድሜ 13.8 ቢሊዮን ዓመታት ነው። የእኛ ፀሐይ እና ምድር የተፈጠሩት ደግሞ ከ4.5 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ነው። ይህ ማለት ከእኛ ምድር መፈጠር በፊት ቢሊዮን ዓመታት ያስቆጠሩ ሌሎች ከዋክብት እና ፈለኮች ነበሩ ማለት ነው።
የእኛን የዕድገት ፍጥነት እና የአጽናፈ ዓለማችንን ዕድሜ አገናኝተን እናስበው። የሰው ልጅ በ10 ሺህ ዓመታት ውስጥ ከድንጋይ ዋሻ ወጥቶ ሮኬቶችን ወደ ጠፈር መላክ ከቻለ፣ ከእኛ ቀደም ብለው ከ1 ሚሊዮን ወይም ከ10 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የተፈጠሩ ስልጣኔዎች ቢኖሩ ኖሮ ምን ደረጃ ላይ ይደርሱ ነበር? ቴክኖሎጂያቸው እጅግ ረቆ፣ ፍኖተ ሃሊብን በሙሉ በማቋረጥ፣ ከተለያዩ ፈለኮች ላይ ሀብት በመሰብሰብ እና ቢያንስ የሬድዮ ሞገዶቻቸው እኛ ጋ ሊደርስ አይገባም ነበር?
እዚህ ላይ ነው ታላቁ እንቆቅልሽ የሚፈጠረው። የሂሳቡ ስሌት፣ የከዋክብቱ ብዛት፣ እና የጊዜው ርዝማኔ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ስልጣኔዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ግልጽ ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል። ጆሯችንን አቅንተን፣ እጅግ የረቀቁ የሬድዮ ቴሌስኮፖችን ወደ ሰማይ አዙረን ድምጻቸውን እንጠብቃለን። እስካሁን ግን፣ ምንም ነገር የለም። ምንም ዓይነት የሬድዮ ሞገድ፣ የሌዘር ብልጭታ፣ ወይም የተጨበጠ ማስረጃ አላገኘንም። ጠፈር ፍጹም እና አስፈሪ ጸጥታ የሰፈነበት ነው።

ደቡብ አፍሪቃ የሚገኙት የሚር ካት የራዲዮ መቀበያ ቴሌስኮፖች
ይህ "ታዲያ ሌሎቹ የት አሉ?" የሚለው ጥያቄ በዓለም የሳይንስ ታሪክ ውስጥ እጅግ አወዛጋቢ የሆነውን ውይይት ፈጥሯል። በቀጣዩ ክፍል (ክፍል 2)፣ በ1950ዎቹ ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ ኤንሪኮ ፈርሚ፣ ከጓደኞቹ ጋር ምሳ እየበላ በድንገት የጠየቀውንና የሳይንስን ዓለም እስካሁን ድረስ ያናወጠውን 'የፈርሚ አያዎ' (The Fermi Paradox) የሚባለውን ታላቅ እንቆቅልሽ በጥልቀት እንመረምራለን።