በስነ-ፈለክ አፍቃሪዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው፣ የካቲት 10፣ 2018 ዓ.ም. የሚከሰተው "ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ" (Annular Solar Eclipse) ቀናት ቀርተውታል። ይህ በተፈጥሮ የሚከሰት አስደናቂ ክስተት፣ ፀሐይን ልክ እንደ "የእሳት ቀለበት" አስመስሎ የሚያሳይ ሲሆን፣ የዚህኛው ዓመት ዋነኛ መድረክ የሚሆነው ደግሞ በረዷማው የአንታርክቲካ ክፍለ ዓለም ነው።
ነገር ግን ይህን ክስተት ከመተንተናችን በፊት፣ ወደ ኋላ መለስ ብለን በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የተከሰተውን ታሪካዊ ክስተት ማስታወሱ ተገቢ ነው።
የላሊበላው ትዝታ፡ ሰኔ 14፣ 2012 ዓ.ም.
ብዙ ኢትዮጵያውያን ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. አይረሱትም። በዚያን ዕለት፣ ሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል፣ በተለይም ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ እና ወልዲያ፣ የዓለም የስነ-ፈለክ ተመራማሪዎች ትኩረት ማዕከል ሆነው ነበር።

ምስል፦ ላልይበላ ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ 2012 ዓ.ም
በወቅቱ የተከሰተው ግርዶሽ ልክ እንደ ዘንድሮው "ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ" ነበር። ጨረቃ በፀሐይ መሃል ስትሆን፣ የፀሐይን ዳርቻዎች ሳትሸፍን በመቅረቷ፣ በሰማይ ላይ ደማቅ እና የሚንቦገቦግ የወርቅ ቀለበት ታይቶ ነበር። ያ የተፈጥሮ ትዕይንት በብዙዎች ዘንድ አስደናቂ እና አስፈሪ ስሜትን የፈጠረ ሲሆን፣ ለሳይንስ ተመራማሪዎች ደግሞ ወርቃማ እድል ነበር።
ሳይንሱ፡ ግርዶሽ እንዴት ይፈጠራል?
የፀሐይ ግርዶሽ ማለት በቀላሉ "የጥላ ጨዋታ" ማለት ነው። ይህ ክስተት እንዲፈጠር ሦስት የሰማይ አካላት (ፀሐይ፣ ጨረቃ እና መሬት) በአንድ ቀጥተኛ መስመር ላይ መሰለፍ አለባቸው።
ነገር ግን ዋናው ሚስጥር ያለው "ርቀት" ላይ ነው።
ጨረቃ ምድርን የምትዞረው ፍጹም ክብ በሆነ መንገድ ሳይሆን፣ ሙልል ባለ ምህዋር ነው። ይህ ማለት ጨረቃ አንዳንዴ ወደ ምድር በጣም ትቀርባለች፣ አንዳንዴ ደግሞ ከምድር በጣም ትርቃለች።
ይህንን በምሳሌ እንመልከት፡ አንድ ሳንቲም አንስተን አይናችን ስር ብናስጠጋው፣ ከፊታችን ያለውን ትልቅ ሕንጻ ሙሉ ለሙሉ ሊጋርደው ይችላል። ያንኑ ሳንቲም እጃችንን ዘርግተን ብናርቀው ግን፣ መጠኑ ያነሰ ስለሚመስል ሕንጻውን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን አይችልም። የፀሐይ ግርዶሽም ልክ እንደዚህ ነው።
ሦስቱ የፀሐይ ግርዶሽ አይነቶች በዝርዝር
በጨረቃ ርቀት እና አሰላለፍ መሰረት ግርዶሾች በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ፡
1. ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ
ይህ "የቀን ጨለማ" የምንለው ነው።
- እንዴት ይፈጠራል? ጨረቃ ምድርን በጣም ቀርባ በምትገኝበት ወቅት፣ መጠኗ ከምድር ሆኖ ሲታይ ትልቅ ይሆናል። በዚህ ጊዜ በፀሐይ ፊት ስታልፍ፣ ፀሐይን ሙሉ ለሙሉ ትሸፍናታለች።
- ምን ይታያል? ፀሐይ ሙሉ ለሙሉ ስለምትጠፋ በቀን ኮከቦች ሊታዩ ይችላሉ። የፀሐይ ውጨኛው የጋዝ ክፍል ብቻ እንደ ነጭ ዘውድ በዳር በኩል ይንቦገቦጋል።

ምስል ፦ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ ምንጭ፦ Eddington's original photograph of the 1919 eclipse ፣ ውክፔዲያ
2. ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ
ይህ "የእሳት ቀለበት" ነው።
- እንዴት ይፈጠራል? ጨረቃ ከምድር በጣም ርቃ በምትገኝበት ወቅት ነው። ጨረቃ ስለራቀች፣ ከምድር ሆና ስትታይ መጠኗ ያነሰ ይመስላል። ልክ እንደ ራቀው ሳንቲም፣ በፀሐይ ፊት ብታልፍም ፀሐይን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን አትችልም።
- ምን ይታያል? የጨረቃ ጥላ የፀሐይን መሃል ብቻ ይሸፍናል፤ የፀሐይ ጠርዞች ግን አይሸፈኑም። በዚህም ምክንያት በሰማይ ላይ ደማቅ የእሳት ቀለበት ይታያል። በሰኔ 2012 ላሊበላ ላይ የታየው ይህ አይነት ነው።

ምስል፦ ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ምንጭ፦ 2012 ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ፣ ላልይበላ ፣ ኢትዮጵያ
3. ከፊል የፀሐይ ግርዶሽ
ይህ "የተገመሰ ዳቦ" የሚመስለው ነው።
- እንዴት ይፈጠራል? ፀሐይ፣ ጨረቃ እና ምድር ፍጹም በአንድ መስመር ሳይሰለፉ ሲቀሩ ነው። ጨረቃ የፀሐይን የተወሰነ ክፍል ብቻ (ከላይ፣ ከታች ወይም ከጎን) ገራድፋ ትወጣለች።
- ምን ይታያል? ፀሐይ ልክ እንደተገመሰ ብስኩት ትታያለች። አብዛኛውን ጊዜ ሙሉ ወይም ቀለበታዊ ግርዶሽ በሚኖርበት አካባቢ፣ ከዋናው መስመር ውጭ ያሉ ሀገራት የሚያዩት ይህንን ከፊል ግርዶሽ ነው።

ምስል፦ ከፊል የፀሐይ ግርዶሽ ምንጭ፦ solar eclipse of 2019 January 6 in Nakhodka, Primorsky Krai, Russia
የየካቲት 10 2018 ግርዶሽ ልዩነት
በዚህ የካቲት ወር የሚከሰተው ግርዶሽ ቀለበታዊ (Annular) ሲሆን፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚከተለው መልኩ ይታያል፡-
የዚህ ግርዶሽ ዋና መተላለፊያ መስመር የሚያልፈው በምድራችን ደቡባዊ ጫፍ በሚገኘው በአንታርክቲካ (Antarctica) የበረዶ አህጉር ላይ ነው። ሙሉውን "የእሳት ቀለበት" ለማየት የሚታደሉት በዚህ አካባቢ የሚገኙ ጥቂት ሳይንቲስቶች እና ፔንጉዊኖች ብቻ ናቸው። በዚህ ቀጠና ውስጥ ቀለበታዊው ቅርጽ ለ2 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ያህል ተጋርዶ ይቆያል።

ምስል፦ የቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሹ ሽፋን በአንታርክቲካ
ከአንታርክቲካ ውጭ፣ የፀሐይ ግርዶሹ በከፊል (Partial Eclipse) በደቡባዊ አፍሪቃ ሀገራት በግልጽ ይታያል። በተለይም በደቡብ አፍሪቃ፣ ናሚቢያ፣ ቦትስዋና፣ ዚምባብዌ፣ ሞዛምቢክ፣ ኤስዋቲኒ፣ ሌሶቶ እና ማዳጋስካር የሚኖሩ ሰዎች ፀሐይ በጨረቃ ተገምሳ ማየት ይችላሉ። የግርዶሹ መጠን እንደ ቦታው ይለያያል፤ ወደ ደቡብ በተጠጋ ቁጥር የሽፋኑ መጠን ይጨምራል።

ምስል፦ የቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሹ ሽፋን በደቡባዊ አፍሪቃ
በተመሳሳይ መልኩ፣ የደቡብ አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍም የዚህ ክስተት ተካፋይ ይሆናል። በዋናነት ቺሊ (Chile) እና አርጀንቲና (Argentina) በከፊል ግርዶሹ ክልል ውስጥ ይካተታሉ። ምንም እንኳን ሙሉውን ቀለበት ባያዩም፣ ፀሐይ በከፊል ተጋርዳ የምትፈጥረውን አስደናቂ እይታ ማስተዋል ይችላሉ።

ምስል፦ የቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሹ ሽፋን በደቡብ አሜሪካ
ቀጥሎስ መቼ ነው?
ግርዶሾች በየዓመቱ ይከሰታሉ፣ ነገር ግን በአንድ ቦታ ላይ ተመልሶ ለመምጣት ብዙ ዓመታትን ይፈጃል።
- ቀጣዩ ቀለበታዊ ግርዶሽ ጥር 29 ፣ 2019 ዓ.ም የሚከሰት ሲሆን፣ በቺሊ፣ አርጀንቲና እና በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ይታያል።
- ለኢትዮጵያውያን ግን፣ እንደ ሰኔ 2012 ዓ.ም. አይነት ግልጽ "የእሳት ቀለበት" ለማየት ረዥም ዓመታትን መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል። እስከዚያው ግን ቴክኖሎጂ በሚፈጥርልን የቀጥታ ስርጭት ከአንታርክቲካ የሚተላለፈውን የዘንድሮን ግርዶሽ መከታተል ይቻላል።
ይህ የሰማይ ላይ ክስተት፣ አጽናፈ ዓለማችን በምን ያህል ጥበብ እና የሂሳብ ቀመር እንደሚንቀሳቀስ የሚያሳየን ህያው ምስክር ነው።