“ህዋ ያለ ድንበር: ዓለምን በትምህርት፣ በሳይንስ እና በበጎ ተግባራት ማስተሳሰር” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ስብሰባ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ ባለሞያዎችን በማሳተፍ ተካሂዷል።
ስብሰባው ትኩረቱን ያደረገው የበጎ አድራጎት በህዋው ማህበረሰብ ፣ በሰው ልጅ የጠፈር በረራ እና ህክምና ላይ በሃገሮች መካከል እየፈጠረ ያለውን ሚና ሲሆን ውይይቱን የመሩት የዩኒቲ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት አሌና ኩዝሜንኮ ናቸው፡፡ የሩስያው ጀግና ኮስሞናንት ኦሌግ ስክሪፖችካ ፤ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኪሩቤል መንበሩ ፤ የናሳ ነርስ ፣ የዩኒቲ ፋውንዴሽን አምባሳደር እና ለሰው ልጅ የጠፈር ተልእኮዎች የሕክምና ድጋፍ ስፔሻሊስት ራክሳና ባትስማኖቫ ፤ በአፍሪካ የጠፈር አመራር ኢንስቲትዩት (ASLI) የትምህርት ፕሮግራሞች አስተባባሪ ኩባኩሩንጊ ሳፊራ እና ሌሎችም ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል::

ወጣቶችን ከህዋ ሳይንስ ጋር የተገናኙ ስራዎች ውስጥ እንዲገቡ እና ለዓለም አቀፍ የትምህርት ትብብሮች በጉልህ እየሰሩ ያሉ እንደ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ (ESSS) ተቋማት በመድረኩ ላይ የተለየ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል::
በሶስት የጠፈር ተልእኮዎች ከ536 ቀናት በላይ በህዋ ላይ የቆዩት እና በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ላይ ለሃገራት ግንኙነት መጠንከር ትልቅ ስራ የሰሩት ሩስያዊ የጠፈር ተመራማሪ ኦሌግ ስክሪፖችካ ዋና ዋና ነጥቦችን አስተላልፈዋል::
የጠፈር ምርምር ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ሳይንቲስቶች፣ መሐንዲሶች እና ተመራማሪዎች የሰው ልጅን የሚጠቅሙ ውጤቶችን ለማግኘት እንዴት በጋራ መስራት እንደሚችሉ ሁሌም ያሳያል።

የህዋ ምርምር በሰዎች መካከል ያለውን ሃገራዊ ድንበር ሳይገድበው ለአንድ ግብ መተማምን፤ መተባበርን፤ እና የእውቀት ልውውጥን መፍጠር የሚችል ልዩ ሁኔታን የሚያመቻች ነገር ነው በማለት ለታዳሚዎች አመላክተዋል::
ከሩሲያ ጋር መተባበራቸው የአፍሪካ ሀገራት ታዛቢዎች ከመሆን ባለፈ በጠፈር ምርምር ዘርፍ ንቁ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።" ካሊል ሉኣቲ
የኑር ስፔስ መስራች ካሊል ሉኣቲ ሩስያ ለህዋ ቴክኖዎሎጂ ለኣለም እያበረከቱ ያለውን ተፅዕኖ እና ሀገራችው በህዋው ዘርፍ አፍሪካ ላይ ቀዳሚ የሚያስብላቸውን ፕሮጀክቶች ለታዳሚዎች ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ውይይቱ የጠፈር ላይ ህክምና ለምድር የጤና አጠባበቅ አስፈላጊነቱን የዳሰሰ ሲሆን ባለሙያዎች ለጠፈር ተመራማሪዎች ታስበው የሚሰሩ ቴክኖሎጂዎች ለህመሟን ማገገሚያ ፣ ለቴሌሜድስን ጨምሮ አዳዲስ መፍትሄዎችን እየፈጠረ መሆኑን አይተዋል::
አዲስ ከሚመጡ የቴክኖሎጂ ስኬቶች ጀርባ የሰው ልጅ ታሪክ ሁሌም እንዳለ ለተሳታፊዎች ያመላከቱት የናሳ ነርስ ለሰው ልጅ የጠፈር ተልእኮዎች የሕክምና ድጋፍ ስፔሻሊስት ራክሳና ባትስማኖቫ ናቸው::
የሰው ልጅ ሁሌም በጠፈር ምርምር መካከል ላይ መቆየት አለበት። ይሄ መርህ ነበር ተመራማሪዎች ወደ መሬት በሚመለሱበት ጊዜ እንድቀበላቸው ስራዬን የሚመራኝ:: በጠፈር ላይ ያለው እያንዳንዱ ስኬት ዋጋ የሚኖረው የሰዎችን ሂወት ማሻሻል የሚችል ከሆነ ብቻ ነው::

ዩኒቲ ፋውንዴሽን ከዓለም አቀፍ ተወካዮች እና ከአንጋፋው የጠፈር ተመራማሪ ኦሌግ ስክሪፖችካ ጋር በመሆን ከተስፋ አዲስ የወላጆች እና የልጅነት ካንሰር ድርጅት (TAPCCO) ጋር በመተባበር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ለሚከታተሉ ህጻናት የህዋ አርት ቴራፒ አዘጋጅተዋል።
ዝግጅቱ ከ18 ሃገራት የተውጣጡ ተሳታፊዎችን ያካተተ የነበረ ሲሆን ይህም በጠፈር፣ በህክምና፣ በጥበብ እና በበጎ ኣድራጎት ያለውን ክፍተት በማጥበብ ለካንሰር ታማሚ ህፃናት እና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ማድረግ ለሚሹ ዓለም አቀፍ ተቋማት አርአያ የሚሆን ትግባር አከናውነዋል:: ህፃናት ስእሎቻቸውን ለተመራማሪዎች ያሳዩ ሲሆን ወደፊት በሚደረጉ የጠፈር ተልእኮዎች ላይ ስእሎቻቸው ወደ ጠፈር እንደሚላኩ ከዚህ በፊት በነበሩ ተልእኮች በሩስያ ካንሰር ታማሚ ህፃናት የተሰሩ ስእሎች እንደተላኩ ተስተውሏል::

ልዑካኑ የምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የስነ-ፈለክ መመልከቻ እንዲሁም የምርምር ማዕከል የሆነውን እንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ (EORC) ፤ የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂዎች፣ የትምህርት እና ፈጠራ ኃላፊነት ያለው የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትን (SSGI) ጎብኝተዋል። ልዑካኑ በሳይንስ ኮሙኒኬሽን ፣ ትምህርት እና በበጎ ፍቃድ የጠፈር ተነሳሽነት ወደፊት ትብብር እንዲደረግ ስምምነት ላይ ለማድረስ ትኩረት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም በተባበሩት መንግስታት አዝጋጅነት አዲስ አበባ ላይ "አዲስ ዓለም: አፍሪካ ለወደፊት የጋራ ራዕይ" በሚል አጀንዳ ሲካሄድ በቆየው ጉባኤ ላይ የሩሲያ ፌዴሬሽን የጠፈር ተመራማሪው ኦሌግ ስክሪፖችካ በመገኘት ስለነበራቸው ቆይታ እና እይታ የተናገሩ ሲሆን "አዲስ ዓለም ለነቃ አንድነት" በሚል መርህ ላይ ያተኮረ ውይይት የስብሰባው ዋና ክስተት ነበር::
