ከህዋ መልስ ቤተሰብ የመሰረቱት "ጠፈርተኛ" አይጦች፡ ለሰው ልጅ ተስፋ የሰጠው አስደናቂ ታሪክ
የሰው ልጅ ወደ ህዋ የሚያደርገው ጉዞ ሁሌም አዳዲስ ታሪኮችን ይዞልን ይመጣል። አሁን ደግሞ ከቻይና የተሰማው ዜና ዓለምን አስገርሟል። አራት አይጦች እንደ ጠፈርተኞች ወደ ህዋ አምርተው ነበር፤ ከነዚህም መካከል አንዷ ወደ ምድር ተመልሳ እናት መሆን ችላለች። ይህ ክስተት ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ከምድር ውጪ ለመኖር ለሚያደርገው የረጅም ጊዜ ህልም ትልቅ ትርጉም አለው።
ነገሩ እንዲህ ነው። በኦክቶበር 31 ቻይና ቁጥር 6፣ 98፣ 154 እና 186 የተሰጣቸውን አራት አይጦች በሼንዙ-21 (Shenzhou-21) የጠፈር መንኮራኩር አማካኝነት ከምድር 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው የጠፈር ጣቢያ ላከች። እነዚህ "ጠፈርተኛ" አይጦች ለሁለት ሳምንታት በህዋ ውስጥ (microgravity)፣ ለጠፈር ጨረር እና ለተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች ተጋልጠው ቆይተዋል። ኖቬምበር 14 በሰላም ወደ ምድር ከተመለሱ በኋላ፣ በዲሴምበር 10 ከሴቶቹ አይጦች አንዷ ዘጠኝ ጤናማ ግልገሎችን ተገላገለች።
ሳይንሱ ምን ይላል?
ከዚህ ቀደም በተደረጉ ሙከራዎች፣ በህዋ የቆየ የአይጥ ዘር (sperm) ምድር ላይ ያሉ ሴት አይጦችን ለማስረገዝ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር። የዚህኛውን ክስተት ለየት የሚያደርገው ግን እንስሳቱ ራሳቸው ወደ ህዋ ሄደው መመለሳቸው ነው። በዚህ አዲስ ጥናት፣ አይጧ ከተገላገለቻቸው ዘጠኝ ግልገሎች ውስጥ ስድስቱ በህይወት መትረፍ ችለዋል፤ ይህም እንደ ተመራማሪዎች ገለጻ መደበኛ የሚባል የመትረፍ መጠን ነው። እናቲቱ ልጆቿን በአግባቡ እያጠባች ሲሆን፣ ግልገሎቹም ንቁ እና በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

(በ2019 ከጠፈር የመጣ የአይጥ ዘር (sperm) በምድር ላይ ያሉ ሴት አይጦችን ለማስረገዝ ጥቅም ላይ ከዋለበት ቀደምት ጥናት የተወሰደ ምስል)
በቻይና የሳይንስ አካዳሚ የእንስሳት ጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ዋንግ ሆንግሜይ (Wang Hongmei)፣ የአጭር ጊዜ የጠፈር ቆይታ የአይጦቹን የመራባት አቅም አለመጉዳቱን ማረጋገጣቸው ለወደፊቱ የጠፈር ምርምር ትልቅ ድል መሆኑን ገልጸዋል።
አይጦቹ ለምን ተመረጡ?
ይህ ተልዕኮ ዝም ብሎ አይጦችን ወደ ጠፈር ለመላክ የተደረገ አይደለም። አይጦች ከሰዎች ጋር ከፍተኛ የሆነ የዘረመል (genetic) ተመሳሳይነት አላቸው። በፍጥነት ይራባሉ፣ እንዲሁም ለተለያዩ አካላዊ ጫናዎች የሚሰጡት ምላሽ ከሰዎች ጋር ይቀራረባል። የጠፈር ቆይታ በአጥቢ እንስሳት የመራባት ሂደት ላይ መሰረታዊ ችግር የሚፈጥር ከሆነ፣ ይህን ቀድመን በእነዚህ አይጦች ላይ ማየት እንችላለን። ይህ ማለት ወደፊት የሰው ልጅ ወደ ማርስ ወይም ጨረቃ ለሚያደርገው ጉዞ እንደ አብነት ያገለግላሉ ማለት ነው።

አራት ግልገሎችን የተገላገለችዋ አይጥ
የአይጦቹን ቆይታ ፈታኝ ያደረገው ክስተት
ጉዞው ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። የሼንዙ-20 (Shenzhou-20) የመመለሻ ጊዜ ሳይታሰብ በመቀየሩ ምክንያት፣ አይጦቹ በጠፈር ጣቢያው ከታሰበው በላይ ረዘም ላለ ጊዜ ለመቆየት ስለተገደዱ የምግብ እጥረት ስጋት ተፈጥሮ ነበር።
በዚህ ጊዜ የምድር ላይ ተመራማሪዎች ቡድን ከጠፈርተኞቹ ጋር በመመካከር ከጠፈርተኞቹ የድንገተኛ የምግብ ራሽን ላይ በመውሰድ ምን መመገብ እንችላለን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሲጥሩ ቆይተዋል። እንደ ብስኩት፣ በቆሎ፣ ሀዘልናት እና የአኩሪ አተር ወተት (soy milk) ያሉ አማራጮች በማቅረብ ለመመገብ በተሰራው ስራ የአኩሪ አተር ወተት ተመራጭ እና አስተማማኝ የድንገተኛ ጊዜ ምግብ ሆኖ አግኝተውታል። በተጨማሪም የሚጠጡት ውሃ ከውጭ በሚገኝ መመገቢያ በኩል ወደ መኖሪያቸው እንዲገባ የተደረገ ሲሆን፣ በ AI (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) የሚታገዝ የክትትል ስርዓት የአይጦቹን እንቅስቃሴ እና አመጋገብ በቅጽበት በመከታተል ምግቡ መቼ እንደሚያልቅ ለመተንበይ ረድቷል።
ከዚህ ጥናት ተመራማሪዎች ምን ይማራሉ?
አሁን ተመራማሪዎች እነዚህን "የጠፈር ግልገሎች" በጥብቅ እየተከታተሉ ነው። የእድገት ደረጃቸውን ከመለካት ባለፈ፣ በእናታቸው የጠፈር ቆይታ ምክንያት የተፈጠሩ ድብቅ የጤና እክሎች መኖር አለመኖራቸውን ያጣራሉ። በተጨማሪም እነዚህ ግልገሎች ራሳቸው ሲያድጉ መራባት ይችሉ እንደሆነ ለማወቅ ጥናት ይደረጋል።
የዚህ ጥናት የመጨረሻ ግብ ከአይጦች ያለፈ ነው። የሰው ልጅ ወደ ማርስ ለሚያደርገው የረጅም ዓመታት ጉዞ ወይም በጨረቃ ላይ ቋሚ ሰፈር ለመመስረት ከመሞከሩ በፊት፣ መራባት በጠፈር ውስጥ ወይም ከጠፈር ቆይታ በኋላ እንዴት እንደሚሆን ማወቅ ያስፈልጋል። አጥቢ እንስሳት በዝቅተኛ ስበት (reduced gravity) ውስጥ መፅነስ እና መውለድ ይችላሉ? የጠፈር ጨረሮች በዘር ላይ ጉዳት ያደርሳሉ? አንዲት አይጥ መውለዷ ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ ባይሆንም፣ ትልቅ ተስፋ ሰጪ ጅምር ነው።