ወደ ጦማር ይመለሱ

በአውሮፓ የእርሻ መሬቶች ላይ የተተከለው ግዙፍ የህዋ መመልከቻ

በአውሮፓ የእርሻ መሬቶች ላይ የተተከለው ግዙፍ የህዋ መመልከቻ

ያልተለመደው የህዋ መመልከቻ

ስለ ቴሌስኮፕ ስናስብ አብዛኛውን ጊዜ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው በተራራ አናት ላይ በሚገኝ ምልከታ ጣቢያ ውስጥ የተገጠመ ግዙፍ የብርጭቆ መስተዋት ወይም ደግሞ እንደ ሀብል እና ጄምስ ዌብ ያሉ የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ዉጤት የሆኑ እና በጠፈር ላይ የሚገኙ ቴሌስኮፖች ናቸው። ለዘመናት ስለ ህዋ ያለን እይታ የተቃኘው የሚታይን ብርሃን ለመያዝ እና የከዋክብትን እንዲሁም የጋላክሲዎችን ጥራት ያላቸው ባለቀለም ፎቶዎች ለማንሳት በተሰሩት በእነዚህ የብርጭቆ እና ብረት ውጤቶች በሆኑ የኦፕቲካል (Optical) ግዙፋን መሳሪያዎች ነበር። ነገር ግን ጽናፈ ዓለም ዓይኖቻችን ከሚያዩት በላይ በብዙ ሌሎች ቋንቋዎች ይናገራል፤ ቀደምት ቴሌስኮፖች ሊያዩአቸው የማይችሉትን ሚስጥሮች የማይታዩ የብርሃን ሞገዶችን በመጠቀም ያስተላልፋል።

የሃብል፣ የዌብ፣ የሮማን እና የሌሎች ታዋቂ ኦብዘርቫቶሪዎች የብርሃን ሞገድ ርዝመት ሽፋን (Wavelength Sensitivity) የሚያሳይ ግራፍ። ምስል ምንጭ: NASA, STScI

Hewa+ Ad
Ad

ከታች በምስሉ ላይ በአውሮፓ የእርሻ መሬቶች ላይ የተበተኑት ነገሮች ተራ አጥር፣ የከብት በረቶች ወይም የሶላር ፓነሎች መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ነገር ግን፣ በዚያ የሚገኘው ተራ የእርሻ ቦታ ሳይሆን በዓለማችን ላይ ካሉ እጅግ ዘመናዊና ሃያል ከሆኑ ሳይንሳዊ መሳሪያዎች አንዱ ነው። ሎፋር (LOFAR - Low-Frequency Array) ያንን የተለመደ የቴሌስኮፕ ምስል ሙሉ በሙሉ ይለውጠዋል። ሎፋር በኔዘርላንድስ ኤክስሎ (Exloo) አቅራቢያ የሚገኝ እና በስምንት የአውሮፓ ሀገራት የተበተኑ የጣቢያ ስብስቦች ያሉት የሬዲዮ ቴሌስኮፕ መረብ ነው። እ.ኤ.አ. በ2010 በኔዘርላንድሷ ንግስት ቤትሪክስ በይፋ የተከፈተው ሎፋር በአለም አቀፍ ጥረት ስም በ ASTRON (የኔዘርላንድስ የሬዲዮ አስትሮኖሚ ተቋም) የሚንቀሳቀስ ነው።

ሎፋር ምንም አይነት ግዙፍ ተንቀሳቃሽ ሰሃኖች ወይም ከባድ ሌንሶች የሉትም። ይልቁንም በየአውሮፓ እርሻዎች ላይ ቋሚ ሆነው የቆሙ ባለሶስት እግር የሽቦ ምሰሶዎች እና ጠፍጣፋ ጥቁር ሳጥኖችን የሚመስሉ ወደ 20,000 የሚጠጉ ቀላል ዳይፖል አንቴናዎችን የያዘ ነው። የስነ-ከዋክብት ተመራማሪዎች አካላዊ ሰሃንን ወደ ህዋ በማዞር ፈንታ፡ ሱፐር ኮምፒውተሮችን በመጠቀም ሎፋርን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ያዞሩታል።

በኔዘርላንድስ የሚገኘው የሎፋር (LOFAR) ራዲዮ ቴሌስኮፕ ኮር ስቴሽን የአየር ላይ እይታ። የምስል ምንጭ፦ © Aerovista Luchtfotografie, Shutterstock

Hewa+ Ad
Ad

ለምን ተገነባ?

ለብዙ አስርት ዓመታት የሬዲዮ አስትሮኖሚ ትኩረት አድርጎ የነበረው ጥራት ያላቸውን ምስሎች ለማንሳት ቀላል በነበሩት አጫጭር የሞገድ ርዝመቶች (ከፍተኛ ፍሪኩዌንሲዎች) ላይ ነበር። ነገር ግን ዝቅተኛው የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ (ከ250 MHz በታች) በአስትሮኖሚ ውስጥ ያልተዳሰሰ የመጨረሻው መስኮት ሆኖ ቆይቶ ነበር።

የ2018 ጥቅል (10 ልዩ ስቲከሮች)
የ2018 ጥቅል (10 ልዩ ስቲከሮች)
የእርስዎ ያድርጉ

የስነ-ከዋክብት ተመራማሪዎች ለመሰረታዊ የኮስሞስ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ይፈልጉ ነበር፡

  • በቀደመው የኮስሞስ የዝግመተ-ለውጥ ደረጃ፣ የመጀመሪያዎቹ ከዋክብት እና ጋላክሲዎች የሃይድሮጅን ጋዝን አዮናይዝ ያደረጉበት "የሪአዮናይዜሽን ዘመን" (Epoch of Reionization) የፊዚክስ ሂደቶች ምን ይመስሉ ነበር?
  • እጅግ ግዙፍ ጥቁር ቀዳዳዎች (supermassive black holes) ቁስ አካልን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የብርሃን ዓመታት ርቀት ላይ በሚያመጥቁበት የሬዲዮ ጄት ሂደት ዉስጥ የሚከናወኑት አስትሮፊዚካዊ ሂደቶች ምን ይመስላሉ?
  • የኮስሚክ መግነጢሳዊ መስኮች (Cosmic Magnetic Fields) አመጣጥ ምንድነው፤ እንዲሁም ከፍተኛ ኃይል ያላቸው የኮስሚክ ጨረሮች በጽናፈ ዓለም ውስጥ እንዴት ይሰራጫሉ?

የቀድሞዎቹ ዝቅተኛ ፍሪኩዌንሲ የሬዲዮ ቴሌስኮፖች በነበራቸው አነስተኛ የመቀበል አቅምና ደካማ የምስል ጥራት (Spatial Resolution) የተገደቡ ነበሩ። በእነዚህ ረጅም የሞገድ ርዝመቶች ላይ ጥራት ያለው ምስል ለማግኘት የሚያስችል ግዙፍ ነጠላ ሰሃን በብቸኝነት መገንባት የማይታሰብ ነበር። የኔዘርላንድስ የሬዲዮ አስትሮኖሚ ተቋም (ASTRON) በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ ሎፋርን እንደ አብዮታዊ "የሶፍትዌር ቴሌስኮፕ" አድርጎ ፀነሰው። በሺዎች የሚቆጠሩ ቋሚ አንቴናዎችን ከ1,000 ኪሎሜትር በላይ በሆነ ሰፊ ርቀት ላይ በመበተንና መረጃዎቻቸውን በዲጂታል መንገድ በማጣመር፡ ሳይንቲስቶች ውጤታማነቱ ወይም የሰሃኑ ስፋት ሙሉ አውሮፓን የሚያክል ምናባዊ ቴሌስኮፕ መፍጠር ቻሉ።

በቅርብ ዓመታት በሎፋር ቴሌስኮፕ አማካኝነት የስነ-ከዋክብት ተመራማሪዎች ቀደም ሲል የማይታወቁና በየጥቂት ደቂቃዎች ወይም ሰዓታት ልዩነት ከፍተኛ የሬዲዮ ሞገድ ብልጭታዎችን የሚልኩ የጠፈር አካላትን ማጥናት ችለዋል።

በኔዘርላንዳዊቷ የስነ-ከዋክብት ተመራማሪ ዶክተር አይሪስ ደ ራውተር እና ባልደረቦቿ የተመራ እና በ2025 (እ.ኤ.አ.) በታዋቂው Nature Astronomy ጆርናል ላይ የታተመው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ እነዚህ ረጅም የጊዜ ዑደት ያላቸው የሬዲዮ ብልጭታኦች (Long-Period Transients) በሁለት ከዋክብት ማለትም በቀይ ድዋርፍ (Red Dwarf) እና በከፍተኛ መግነጢሳዊ ኃይል ባለው ነጭ ድዋርፍ (White Dwarf) የመግነጢሳዊ መስክ ውህደት እና መስተጋብር ምክንያት እንደሚፈጠሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ማረጋገጥ ተችሏል።

Hewa+ Ad
Ad

 እንዴት ይሰራል?

ሎፋር በ 10 MHz እና 240 MHz መካከል ያሉ ዝቅተኛ ፍሪኩዌንሲ ያላቸውን የሬዲዮ ሞገዶች (ከ1.3 ሜትር እስከ 30 ሜትር የሚደርሱ የሞገድ ርዝመቶች) ያጠናል።

እያንዳንዱ የሎፋር ጣቢያ ሁለት የተለያየ ዓይነት ያላቸውን የሴንሰር ስብስቦች ይዟል፡

የኢ.ስ.ሳ.ሶ ሎጎ ስቲከር ጥቅል
የኢ.ስ.ሳ.ሶ ሎጎ ስቲከር ጥቅል
የእርስዎ ያድርጉ
  • ዝቅተኛ ባንድ አንቴናዎች (Low Band Antennas - LBA): ከ 10 እስከ 80 MHz ፍሪኩዌንሲ የተመቻቹ ቀላል ሸረሪት መሰል አንቴናዎች። በዋናነትም በጣም ሩቅ የሆነውን ቀደማይ ጽናፈ ዓለም እንዲሁም የኮስሚክ ጨረሮችን ለማጥናት የሚያገለግሉ ናቸው። 
  • ከፍተኛ ባንድ አንቴናዎች (High Band Antennas - HBA): ከ 120 እስከ 240 MHz የተመቻቹ እና የዳይፖል ስብስቦችን የያዙ ጠፍጣፋ ጥቁር ሳጥኖች። ትኩረታቸውም የጥልቅ ሰማይ ጥናቶች፣ ከዋክብት የሚፈጠሩባቸው ጋላክሲዎች እና ጥቁር ቀዳዳዎችን በማንሳት ላይ ያተኮረ ነው።

በኔዘርላንድስ የሚገኘው የLOFAR ቴሌስኮፕ ዝቅተኛ ፍሪኩዌንሲ አንቴናዎች (LBA)። የምስል ምንጭ፦ ASTRON

ሎፋር አንቴናዎቹን በአካል ከማዞር ይልቅ፣ የበርካታ አንቴናዎችን መረጃ አጣጥሞ እንደ አንድ ግዙፍ ምናባዊ ቴሌስኮፕ የሚያሰራውን "ኢንተርፌሮሜትሪ” እና ዲጂታል የሞገድ አቅጣጫ መቆጣጠሪያን (digital beamforming) በማቀናጀት ይሰራል።

  1. ምልክቶችን መቀበል : የሬዲዮ ምልክቶች በሁሉም አቅጣጫ ባሉ አንቴናዎች ላይ በቅርብ የጊዜ ልዩነት ይደርሳሉ።
  2. ወደ ዲጂታል መቀየር: በጣቢያው ያሉ ኤሌክትሮኒክሶች የቮልቴጅ ምልክቶቹን ወዲያውኑ ወደ ዲጂታል ይለውጣሉ።
  3. በፋይበር ኦፕቲክ ማስተላለፍ: መረጃዎች በከፍተኛ ፍጥነት ባላቸው ኦፕቲካል ፋይበሮች በኩል በኔዘርላንድስ ግሮኒንገን ወደሚገኙ ማዕከላዊ ሱፐር ኮምፒውተሮች ይላካሉ።
  4. በሶፍትዌር ማጣመር: ሱፐር ኮምፒውተሮች በአንቴናዎቹ መካከል ያለውን የጊዜ ልዩነት በማጣመር አደራደሩን በሰማይ ላይ በሚፈለገው ማንኛውም ቦታ ላይ "እንዲያተኩር" ያደርጉታል።

ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

ሎፋር በበርካታ ልዩ ችሎታዎቹ ምክንያት በምድር ላይ ካሉ ከደረጃው በላይ ከሆኑ ሌሎች ምልከታ ጣቢያዎች ሁሉ ተለይቶ ይቆማል፡

  • እጅግ ሰፊ የሆነ የማየት አቅም: ነጠላ አንቴናዎቹ ወደ ሁሉም አቅጣጫ የሚያዩ በመሆናቸው ሎፋር በአንድ ጊዜ ሰፊ የሰማይ አካባቢን ማየት ይችላል።
  • በአንድ ጊዜ በብዙ አቅጣጫ ማየት: ሎፋር በአንድ ጊዜ እስከ 8 ሙሉ በሙሉ የተለያዩ አቅጣጫዎችን ማየት ይችላል፤ ይህም ሳይንቲስቶች የፀሐይ ፍንዳታዎችን እየተከታተሉ በተመሳሳይ ጊዜ ሩቅ ያሉ ጋላክሲዎችን እንዲያጠኑ ያስችላቸዋል።
  • በዝቅተኛ ፍሪኩዌንሲ ከፍተኛ ጥራት ያለው ምስል ማግኘት: በጀርመን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ፣ ስዊድን፣ አየርላንድ፣ ላቲቪያ እና ጣሊያን የሚገኙ አለምአቀፍ ጣቢያዎችን በኔዘርላንድስ ከሚገኙት ዋና ጣቢያዎች ጋር በማገናኘት ሎፋር በረጅም የሬዲዮ ሞገዶች ላይ ወደር የሌለው ጥራት ያለው ምስል ያመነጫል።
  • ወዲያውኑ አቅጣጫን መቀየር: ሙሉ በሙሉ በሶፍትዌር የሚቆጣጠር መሆኑ ሎፋር በሰማይ ላይ እንደ ፈጣን የሬዲዮ ፍንዳታዎች (FRBs) ወይም የፀሐይ ፀሐይ ብልጭታዎች ያሉ አጫጭር ክስተቶችን ለመያዝ ወዲያውኑ አቅጣጫውን እንዲቀይር ያስችለዋል።

በ LOFAR የተከናወኑ ዋና ዋና ምርምሮች

ሎፋር ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በአስትሮፊዚክስ ዘርፍ ከፍተኛ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡

  1. የሎፋር የሁለት ሜትር ሰማይ ጥናት (LoTSS - LOFAR Two-metre Sky Survey): ይህ ዋና ጥናት ከዚህ ቀደም የማይታወቁ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሰማይ አካላትን ካርታ አውጥቷል። በሁለተኛው የመረጃ ልቀቱ (LoTSS-DR2) ሳይንቲስቶች ከ 4.4 ሚሊዮን በላይ የሬዲዮ ምንጮችን ይፋ ያደረጉ ሲሆን አብዛኛዎቹ በሩቅ ጋላክሲዎች ውስጥ የሚገኙ ግዙፍ ጥቁር ቀዳዳዎች ወይም ፈጣን የከዋክብት ምስረታ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ናቸው።
  2. የከዋክብት ምስረታን ለማጥናት የኮስሚክ አቧራን (የከዋክብትን ብርሃን የሚጋርዱ የህዋ ቅንጣቶችን) ሰብሮ መግባት: ከዋክብት ከሚፈጠሩባቸው ቦታዎች የሚወጣው የኦፕቲካል ብርሃን ብዙ ጊዜ በከዋክብት መካከል ባሉ ወፍራም የአቧራ ደመናዎች ይጋረጣል። የሬዲዮ ሞገዶች ግን ይህንን አቧራ ሰብረው ያልፋሉ። የ ሎፋር ጥልቅ ምስሎች በጥንታዊው ጽናፈ ዓለም ውስጥ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሚልኪ ዌይን የሚመስሉ ጋላክሲዎችን የለዩ ሲሆን፡ ይህም ስለ ኮስሚክ ከዋክብት ምስረታ ታሪክ ግልጽ የሆነ የጊዜ መስመር እንዲኖረን አድርጓል።
  3. የኮስሚክ ጨረር ፊዚክስ እና የከባቢ አየር ፊዚክስ: እጅግ ከፍተኛ ኃይል ያላቸው የኮስሚክ ጨረሮች የምድርን የላይኛው ከባቢ አየር ሲመቱ፣ አጫጭር የሬዲዮ ሞገዶችን የሚያመንጩ ሁለተኛ ደረጃ ቅንጣቶች ይፈጠራሉ። LOFAR እነዚህን የሬዲዮ ፍንዳታዎች በናኖሰከንድ ትክክለኛነት በመቅረጽ፣ የቅንጣቶቹን የኃይል መጠን እና ኬሚካላዊ ይዘት ለመተንተን ያግዛል።
  4. የህዋ አየር ሁኔታ ማለትም በፀሐይ እንቅስቃሴዎች (እንደ ኃይለኛ ጨረሮች፣ የፕላዝማ ልቀቶች እና የፀሐይ ነፋሳት) ምክንያት በምድር አቅራቢያና በጠፈር አካባቢ የሚከሰቱ የማግኔቲክ እና የጨረራ ለውጦች እንዲሁም የኤክሶ-ፕላኔት ጥቆማዎች: ሎፋር በምድር ላይ የጂኦማግኔቲክ አውሎ ነፋሶችን ሊያስከትሉ የሚችሉ የፀሐይ ፕላዝማ ልቀቶችን (CMEs) ለመከታተል ፀሐይን ይከታተላል። በተጨማሪም ሎፋር በቅርብ ከሚገኙ ቀይ ድዋርፍ ከዋክብት (እንደ CR Draconis ያሉ) የሬዲዮ ልቀቶችን የለየ ሲሆን ይህም በከዋክብት እና በፕላኔቶቻቸው ብመካከል ስላለው ማግኔቲክ ግንኙነት ጥቆማዎችን ሰጥቷል።

የሎፋር የሁለት ሜትር የሰማይ ቅኝት (LoTSS) የሽፋን ካርታ። በሰሜናዊው የሰማይ ክፍል የተደረጉ የቅኝት ክልሎችን (በጥቁር መስመር የተከለሉ)፣ የጥልቅ መስክ ምርምር ቦታዎችን (በብጫ የተከለሉ) እና የራዲዮ ሞገድ መጠን ያሳያል። የምስል ምንጭ፡ ASTRON / LOFAR Surveys Collaboration

የኢ.ስ.ሳ.ሶ ባለቀለም ስቲከር ጥቅል
የኢ.ስ.ሳ.ሶ ባለቀለም ስቲከር ጥቅል
የእርስዎ ያድርጉ

የቴክኖሎጂው ቀጣይ ምዕራፍ

ሎፋር 2.0 (LOFAR 2.0) በመባል የሚታወቅ ትልቅ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህ ማሻሻያ ኤሌክትሮኒክስ እና የመቀበያ መሳሪያዎችን የሚያዘምን ሲሆን፣ በ LBA (Low Band Antenna - ዝቅተኛ የፍሪኩዌንሲ ባንድ አንቴና፤ ከ10 እስከ 90 MHz) እና በ HBA (High Band Antenna - ከፍተኛ የፍሪኩዌንሲ ባንድ አንቴና፤ ከ110 እስከ 240 MHz) በአንድ ጊዜ ለመመልከት፣ የመለኪያ ባንድዊድዝ (በአንድ ጊዜ የሚለካው ዝቅተኛው እና ከፍተኛው ፍሪኩዌንሲ መካከል ያለው ልዩነት) ለማስፋት እና የመረጃ ማቀናበር ፍጥነትን በከፍተኛ ደረጃ ለመጨመር ያስችላል። በጃንዋሪ 2024 ሎፋር ወደ አውሮፓ የምርምር መሰረተ ልማት ጥረት (LOFAR ERIC) የተሸጋገረ ሲሆን፡ ይህም በመላው አውሮፓ የረጅም ጊዜ የፋይናንስ እና የትብብር የምርምር አጋርነቶችን አጠናክሯል።

ሎፋር በአሁኑ ጊዜ በአውስትራሊያ እና ደቡብ አፍሪካ በመገንባት ላይ ላለው እና የአለም ትልቁ የሬዲዮ ምልከታ ጣቢያ ለሆነው ስኩዌር ኪሎሜትር አሬይ (SKA) እንደ ዋና ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ መንገድ ጠራጊ ሆኖ ያገለግላል። ከ ሎፋር የሶፍትዌር መዋቅር፣ የቢግ ዳታ ማቀናበሪያ እና የጣቢያ ንድፍ የተገኙ ትምህርቶች የአለምአቀፍ የሬዲዮ አስትሮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታን በቀጥታ እየቀረጹ ይገኛሉ።


በመጨረሻም የሎፋርን አቅም በመጠቀም ምርምር ከሚያካሂዱ ቡድኖች መካከል አስትሮፍላሽ (AstroFlash) በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው። ይህ ዓለም አቀፍ የምርምር ቡድን የሕዋን ምስጢራት ለመመርመር ፈጣን የሬዲዮ ፍንዳታዎችን (fast radio transients) በመተንተን ላይ ያተኩራል ከ McGill University፣ University of Amsterdam፣ ASTRON፣ እና JIVE የተወጣጡ ሳይንቲስቶችን ያቀፈው ይህ የጥናት ቡድን፣ በከፍተኛ ፍጥነት እና በብዙ ፍሪኩዌንሲዎች በሚደረጉ የሬዲዮ ምልከታዎች ላይ እየሰራ ይገኛል። የሎፋርን አቅም በመጠቀም ምርምር ከሚያካሂዱ ቡድኖች መካከል አስትሮፍላሽ (AstroFlash) በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው። ይህ ዓለም አቀፍ የምርምር ቡድን የሕዋን ምስጢራት ለመመርመር ፈጣን የሬዲዮ ፍንዳታዎችን (fast radio transients) በመተንተን ላይ ያተኩራል ከ McGill University፣ University of Amsterdam፣ ASTRON፣ እና JIVE የተወጣጡ ሳይንቲስቶችን ያቀፈው ይህ የጥናት ቡድን፣ በከፍተኛ ፍጥነት እና በብዙ ፍሪኩዌንሲዎች በሚደረጉ የሬዲዮ ምልከታዎች ላይ እየሰራ ይገኛል። 

ሎፋር እና መሰል የሬዲዮ ቴሌስኮፖች የታገዙ ፈጣን የራዲዮ ክስተቶችን እና የኮስሚክ ፍንዳታዎችን በመመርመር ላይ የሚገኙት የአስትሮፍላሽ ቡድን አባላት። ምንጭ፡ https://astroflash-frb.github.io/

🔗 Sources

LOFAR ERIC Announcement: Thüringer Landessternwarte (TLS) News LOFAR Surveys & Datasets: LOFAR Surveys Web Portal Operating Organization: ASTRON (Netherlands Institute for Radio Astronomy) Transient Science Research: AstroFlash Collaboration Page

ሰዎች እነዚህንም ወደዋል

Hewa+ አሁን በAndroid ላይ ይገኛል!

ከGoogle Play Store ያግኙት

መተግበሪያውን ያውርዱ