ወደ ጦማር ይመለሱ

የምዕራብ ሰማይ ድንቅ ትዕይንት፡ የዝሁራ እና መሽተሪ ማራኪ ግጥምጥሞሽ

የምዕራብ ሰማይ ድንቅ ትዕይንት፡ የዝሁራ እና መሽተሪ ማራኪ ግጥምጥሞሽ

እንዴት፣ መቼ እና የት መመልከት እንችላለን?

ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ወደ ምዕራብ ሰማይ ስንመለከት ጎልተው የሚታዩ ሁለት ደማቅ አካላት አሉ። ብዙ ጊዜ ከሰዎች "እነዚህ ደማቅ ብርሃኖች ምንድን ናቸው?" የሚል ጥያቄ ይነሳል። እነዚህ በሰማያችን ላይ ከሚታዩት ፈለኮች (planets) ሁሉ ደማቅ የሆኑት መሽተሪ (Jupiter) እና ዝሁራ (Venus) ናቸው።

ባለፉት ቀናት በምዕራብ ሰማይ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀራረቡ የመጡት እነዚህ ፈለኮች፣ ዛሬ ማታ እጅግ በጣም ተጠግተው ይገናኛሉ።

መሽተሪ ( በግራ በኩል ) እና ዝሁራ ( በቀኝ በኩል) በምዕራብ ሰማይ ላይ ፤ ፀሐይ እንደጠለቀች

መቼ እና ከስንት ሰዓት እስከ ስንት ሰዓት መመልከት እንችላለን?

ይህንን ትዕይንት ለመመልከት የተለየ የህዋ መነጽር (ቴሌስኮፕ) አያስፈልገንም፤ በዓይናችን በቀላሉ ልናየው እንችላለን።

  • የት አቅጣጫ? ፀሐይ ወደ ጠለቀችበት አቅጣጫ ትክክል ወደ ምዕራብ ሰማይ እንመልከት።
  • ከስንት ሰዓት ጀምሮ? ፀሐይ ከጠለቀችበት ጊዜ አንስቶ (ከምሽቱ 12፡40 ገደማ ጀምሮ) ሰማዩ እየጨለመ ሲመጣ በግልጽ መታየት ይጀምራሉ።
  • እስከ ስንት ሰዓት? ፈለኮቹ ልክ እንደ ፀሐይ ቀስ እያሉ ወደ ምዕራብ አድማስ ስለሚጠልቁ፣ ከምሽቱ 2፡30 እስከ 3፡00 ባለው ጊዜ ውስጥ ከአድማስ በታች ይገባሉ። ስለዚህ ትዕይንቱን ለመመልከት ትክክለኛው ሰዓት ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ነው።

በዚህ ምሽት በመካከላቸው ያለው ርቀት ወደ 1.6 ዲግሪ (የሙሉ ጨረቃን ስፋት ሶስት እጥፍ ያህል) ብቻ ይጠጋል። አጉሊ መነጽር ካለን ደግሞ ሁለቱንም በአንድ እይታ ውስጥ አጠቃልለን ማየት እንችላለን።

በሰማይ ላይ የምናየው ፈለክ መሆኑን እንዴት መለየት እንችላለን?

ብዙ ጊዜ ሰዎች በሰማይ ላይ የሚያዩትን ደማቅ ብርሃን ኮከብ ነው ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ኮከብን ከፈለክ መለየት ቀላል ነው፡-

  1. የብርሃን መብለጭለጭ (Twinkling): ከዋክብት ከእኛ በጣም የራቁ በመሆናቸው ብርሃናቸው የመሬትን ከባቢ አየር አቋርጦ ሲመጣ ይረበሻል፤ በዚህም ምክንያት ይብለጨለጫሉ (ዓይን እንደሚጠቅስ ብርሃን)። ፈለኮች ግን ወደ እኛ ቅርብ ስለሆኑ ብርሃናቸው የተረጋጋ እና የማይብለጨለጭ ቀጣይነት ያለው ነጸብራቅ ይሰጣል።
  2. ደማቅነት: ዛሬ ማታ የምናያቸው አካላት በሰማይ ላይ ከሚገኙት ከዋክብት ሁሉ እጅግ በጣም ደማቆች ናቸው። ዝሁራ (Venus) ከሁለቱ ይበልጥ ደማቅ ስትሆን (በ -4 ማግኒቲዩድ ታበራለች)፣ ከእሷ አጠገብ ያለችው መሽተሪ (Jupiter) ደግሞ በትንሹ አንሳ ትታያለች (-2 ማግኒቲዩድ)።

ስለዚህ፣ በምዕራብ ሰማይ ላይ የማይብለጨለጭ፣ የተረጋጋ እና እጅግ ደማቅ ብርሃን የሚያመነጩ ሁለት አካላትን ካየን፤ እያየን ያለነው ዝሁራን እና መሽተሪን መሆኑን እርግጠኛ መሆን እንችላለን።

ይህ ክስተት በምን ምክንያት ይፈጠራል? የተለመደስ ነው?

ይህ ክስተት በሥነ-ፈለክ አጠራር "ግጥምጥሞሽ" (Conjunction) ይባላል። ፈለኮች ፀሐይን የሚዞሩት በተለያየ ፍጥነት እና ርቀት ላይ ነው። ዝሁራ ከፀሐይ ቅርብ ስለሆነች ፈጣን ዙረት አላት፤ መሽተሪ ደግሞ ሩቅ በመሆኗ ቀስ ብላ ትዞራለች። ልክ በሩጫ ትራክ ላይ ፈጣኑ ሯጭ ቀርፋፋውን እንደሚቀድመው ሁሉ፣ ዝሁራም በመሽተሪ ፊት ለፊት በምታልፍበት ጊዜ፣ ከመሬት ላይ ሆነን ስናያቸው በአንድ መስመር ላይ የተሰለፉ መስለው ይታዩናል።

ይህ ክስተት የተለመደ ነው ወይ? አዎ፣ የዝሁራ እና መሽተሪ መገናኘት አልፎ አልፎ የሚከሰት አይደለም፤ በየ 1 እና 2 ዓመቱ መካከል ይከሰታል። ነገር ግን ልክ እንደ ዛሬው ማታ ከፀሐይ ርቀው፣ ሰማይ ላይ እጅግ በጣም ተቀራርበው በግልጽ መታየታቸው የዛሬውን ትዕይንት ይበልጥ ማራኪ ያደርገዋል።

አስገራሚው የርቀት እውነታ

የምናየው ይህ ትዕይንት ከመሬት እይታ አንጻር ብቻ የተፈጠረ መሆኑን ማወቅ ያስገርማል። ዛሬ ማታ ሰማይ ላይ ስናያቸው የተነካኩ ቢመስሉም በእውነቱ በመካከላቸው ሰፊ የጠፈር ላይ ርቀት አለ።

መሽተሪ (Jupiter) ከመሬት 905 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስትገኝ፣ ዝሁራ (Venus) ግን ከመሽተሪ አምስት እጥፍ ወደ እኛ ትቀርባለች። የፀሐይ ብርሃን ዝሁራ ላይ ደርሶ ወደ እኛ ለመንፀባረቅ 10 ደቂቃ ብቻ ሲፈጅበት፣ ከመሽተሪ ለመምጣት ግን 50 ደቂቃዎችን ይወስዳል!

በዚህ ወቅት የሚጠበቁ ቀጣይ የህዋ ላይ ትዕይንቶች

ይህ ክስተት ከተፈጠረ በኋላም በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ሌሎች ተያያዥ ክስተቶች ይጠበቃሉ፡

ማጠቃለያ

እነዚህን ፈለኮች ዝም ብለን ከማየት አልፈን፣ ከእኛ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀው በራሳቸው ምህዋር ላይ እየተሽከረከሩ መሆናቸውን ማሰቡ ራሱ የህዋን አስገራሚነት ያሳያናል።

ስለዚህ፣ ዛሬ ምሽት ፀሐይ ስትጠልቅ በሞባይል ስልኮቻችንን የህዋ (Hewa+) መተግበሪያን በመጠቀም ወደ ምዕራብ ሰማይ እንመልከት፤ የነዚህን ሁለት ደማቅ ፈለኮች ውብ እንቅስቃሴ እና የጠፈርን ድንቅ ስራ መመልከት እንዳያመልጠን!

ሰዎች እነዚህንም ወደዋል

Hewa+ አሁን በAndroid ላይ ይገኛል!

ከGoogle Play Store ያግኙት

መተግበሪያውን ያውርዱ