ወደ ጦማር ይመለሱ

አዳዲስ ጥናቶች መሪህ በአንድ ወቅት ከምድር አርክቲክ ውቅያኖስ የሚበልጥ ውሃ እንደነበራት አረጋገጡ

አዳዲስ ጥናቶች መሪህ በአንድ ወቅት ከምድር አርክቲክ ውቅያኖስ የሚበልጥ ውሃ እንደነበራት አረጋገጡ

ዛሬ ላይ መሪህ ደረቅ፣ ቀዝቃዛ እና አቧራማ በመሆኗ ቀይዋ ፕላኔት በመባል በሰፊው ትታወቃለች። ላዩን ሲያዩት በፕላኔቷ ላይ ከበረዶ በስተቀር ምንም አይነት ፈሳሽ ውሃ ሊኖር አይችልም ብሎ ማሰብ ተፈጥሯዊ ነው። ነገር ግን ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የጠፈር እና ስነ-ምድር ሳይንቲስቶች ባደረጉት አዳዲስ ጥናቶች መሰረት፣ መሪህ ከቢሊዮኖች ዓመታት በፊት ፈጽሞ የተለየች፣ ሞቃታማ፣ ጥቅጥቅ ያለ ከባቢ አየር እና በገጽታዋ ላይ የሚፈስ ውሃ የነበራት ፕላኔት ነበረች።

ግዙፉ የመሪህ ውቅያኖስ እና የውሃው መጠን

ከአራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዓመታት በፊት መሪህ ፕላኔቷን በሙሉ ሊሸፍን የሚችል፣ ከሶስት መቶ ሜትር እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ጥልቀት ያለው ውቅያኖስ ነበራት። በተለይም በሰሜናዊው የፕላኔቷ ዝቅተኛ ክፍል የነበረው ግዙፍ ውቅያኖስ አስራ ዘጠኝ በመቶ የሚሆነውን የፕላኔቷን ገጽታ የሸፈነ ሲሆን፣ የውሃ መጠኑም በምድር ላይ ከሚገኘው የአርክቲክ ውቅያኖስ ይበልጥ ነበር።

በመሪህ የሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ነበረ ተብሎ የሚታሰበው ውቅያኖስ

ይህን ለማወቅ የናሳ ሳይንቲስቶች በምድር ላይ ያሉ ግዙፍ ቴሌስኮፖችን በመጠቀም በመሪህ ከባቢ አየር ውስጥ የሚገኙትን የተለያየ ክብደት ያላቸውን የውሃ ቅንጣቶች አጥንተዋል። የናሳ መሪ ተመራማሪ ጀሮኒሞ ቪላኑዌቫ እንዳብራሩት፣ በአሁኑ ጊዜ በመሪህ ላይ የሚገኘውን ከባድ ውሃ እና መደበኛ ውሃ በማነጻጸር ጥንታዊቷ መሪህ ምን ያህል ውሃ እንደነበራት ትክክለኛ ግምት ማስቀመጥ ተችሏል። በተጨማሪም ሌሎች ተመራማሪዎች ከመሪህ ተገንጥለው በመጡ እና በእድሜ እጅግ አንጋፋ በሆኑ የከዋክብት ድንጋዮች ውስጥ ያለውን የክሮሚየም አይሶቶፕ መጠን በመመርመር ይህንኑ ግዙፍ የውሃ መጠን አረጋግጠዋል።

በድንጋይ ላይ የተቀረጸው የውሃ ታሪክ እና የወንዝ ዴልታዎች

የዚህ ጥንታዊ የውሃ አካል ማስረጃዎች ዛሬም ድረስ በመሪህ ገጽታ ላይ በግልጽ ይታያሉ። በአርካንሳስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆነው ኮሪ ሂዩዝ እና የጥናት ቡድኑ፣ በመሪህ ኤኦሊስ ዶርሳ በሚባል አካባቢ የሚገኙትን የደረቁ የወንዝ ዴልታዎች ቅርጽ አጥንተዋል። እነዚህ ቅርጾች በአሜሪካ አርካንሳስ ግዛት ውስጥ ከሶስት መቶ ሚሊዮን ዓመታት በፊት ከተፈጠረው የዌዲንግተን አሸዋማ ድንጋይ አወቃቀር ጋር በግሩም ሁኔታ ይመሳሰላሉ።

የአውሮፓ የጠፈር ኤጀንሲ (ESA) 'መሪህ ኤክስፕረስ' መንኮራኩር በመሪህ ገጽታ ላይ ወደ 700 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ጥንታዊ የደረቀ የወንዝ ስርአትን የሚያሳይ ይህንን ምስል አነሳች። (ምንጭ/Credit፦ ESA/Björn Schreiner/FU Berlin)

በምድር ላይ ወንዞች ወደ ውቅያኖስ ለመቀላቀል ሲቃረቡ ፍጥነታቸው ስለሚቀንስ አሸዋ እና ጭቃ ያከማቻሉ። ወንዙ ሲደርቅ ይህ ጭቃ ወደ ጠንካራ ድንጋይነት ይቀየራል፤ በጊዜ ሂደትም በነፋስ እና ዝናብ ሲጠረግ የድሮው የወንዝ መስመር ልክ እንደ ኮረብታ ከፍ ብሎ ይታያል። በመሪህ ላይ የተገኘውም ልክ እንደዚህ አይነት ጥንታዊ የውሃ ፍሰት ዱካ ሲሆን፣ ይህም የመሪህ ወንዞች ፍጥነታቸውን እየቀነሱ ወደ አንድ ትልቅ ውቅያኖስ ይገቡ እንደነበር ጠንካራ ማሳያ ነው።

ይህ ሁሉ ውሃ የት ገባ?

ታዲያ መሪህ ይህን ያህል የውሃ ማከማቻ ከነበራት ዛሬ ላይ ውሃው የት ገባ?

መሪህ ከጊዜ በኋላ መግነጢሳዊ መስኳን ስታጣ፣ ከፀሀይ የሚመነጨው አደገኛ እና ሀይለኛ ንፋስ የፕላኔቷን ከባቢ አየር ቀስ በቀስ ጠረገው። ከባቢ አየሩ ሲሳሳ ወንዞቹ መድረቅ ጀመሩ። መረጃዎች እንደሚያሳዩት መሪህ ሰማንያ ሰባት በመቶ የሚሆነውን ውሃዋን ተነኖ ወደ ህዋ እንዲያመልጥ አድርጋለች። የተቀረው አነስተኛ ውሃ ደግሞ በፕላኔቷ የሰሜን እና ደቡብ ዋልታዎች ላይ በበረዶ መልክ ተከማችቶ ይገኛል።

ከምድር በፊት የጀመረ ህይወት ሊኖር ይችላል?

ይህ ግኝት ስለ ህይወት አመጣጥ ያለንን ግንዛቤ ሙሉ በሙሉ ሊቀይረው ይችላል። መሪህ ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ እና በከዋክብት ድንጋዮች አማካኝነት የመጡ እንደ አሚኖ አሲድ ያሉ ለህይወት መፈጠር መሰረታዊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በነበሯት ጊዜ፣ ምድር ገና ትኩስ እና ህይወት አልባ ነበረች።

በዚያን ወቅት ምድር ጨረቃን ከፈጠረው ግዙፍ ግጭት እያገገመች እና ማናቸውንም የህይወት ጭላንጭሎች ባጣችበት ሰዓት፣ መሪህ በመጀመሪያዎቹ አንድ መቶ ሚሊዮን ዓመታት ውስጥ ለህይወት እጅግ ምቹ የሆነች ፕላኔት ነበረች። ውሃ ባለበት ቦታ ሁሉ ህይወት ሊኖር ስለሚችል፣ በስርአተ ፀሀያችን ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ህይወት ያላቸው ነገሮች የተፈጠሩት ከምድር በፊት በመሪህ ላይ ሊሆን ይችላል የሚል ጠንካራ ሳይንሳዊ ግምት አለ። ይህን ታላቅ ምስጢር ለመፍታትም ወደፊት ወደ መሪህ የሚደረጉ ጉዞዎች ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

ሰዎች እነዚህንም ወደዋል

Hewa+ አሁን በAndroid ላይ ይገኛል!

ከGoogle Play Store ያግኙት

መተግበሪያውን ያውርዱ