Back to Blog

በአውሮጳ የታየው የሰማይ ላይ ፍንዳታ

በአውሮጳ የታየው የሰማይ ላይ ፍንዳታ

እሁድ፣ የካቲት 29፣ 2018 ዓ.ም (ማርች 8፣ 2026 እ.ኤ.አ) ከምሽቱ 12፡55 አካባቢ (18:55 CET) በአውሮጳ ሰማይ ላይ (በተለይም በጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ሉክሰምበርግ እና ኔዘርላንድስ) አንድ ያልተለመደ እና አስደናቂ ክስተት ታይቷል። ከደቡብ ምዕራብ ወደ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ሲጓዝ የታየው ይህ የእሳት ኳስ (Fireball) ለ6 ሰከንዶች ያህል ሰማዩን አብርቶት፣ ከፈነዳ በኋላ የሚታይ ዱካ ትቶ አልፏል።

ክስተቱ እንደ አውሮጳውያን 'AllSky7' ባሉ ልዩ የሜትዮር ካሜራዎች እና በተንቀሳቃሽ ስልኮች የተቀረጸ ሲሆን፣ በአንዳንድ ስፍራዎች የፍንዳታው ድምፅ ከመሬት ሆኖ ሊሰማ ችሏል። አልፎ ተርፎም በጀርመን ኮብለንዝ-ጉልስ (Koblenz-Güls) ከተማ ቢያንስ አንድ የመኖሪያ ቤት በሜትዮራይቱ ስባሪዎች ተመትቷል፤ ሆኖም በሰው ላይ የደረሰ አንዳችም ጉዳት አልተመዘገበም።

የአውሮጳ የጠፈር ኤጀንሲ (ESA) የፈለካዊ መከላከያ ቡድን (Planetary Defence team) እንዳስታወቀው፣ ይህ የሕዋ አካል መጠኑ ጥቂት ሜትሮች ብቻ እንደነበር ይገመታል። ይህ ክስተት ግን አንድ ትልቅ እና አሳሳቢ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡ ወደ መሬት የሚመጡ አደገኛ የሕዋ አካላትን አስቀድመን መለየት ለምን ይከብደናል?

ይህን ጥልቅ ጉዳይ ከመመልከታችን በፊት፣ በሰማይ ላይ የምናያቸው እነዚህ አካላት በሳይንሱ ምን ተብለው እንደሚመደቡ በአጭሩ እንመልከት፡-

ሜትዮሮይድ (Meteoroid)፡ ለመሬት ምህዋር በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው በጠፈር ላይ የሚጓዙ ዓለቶች ወይም ድንጋዮች ናቸው።

ሜትዮር (Meteor)፡ በተለምዶ “ተወርዋሪ ኮከብ” በመባል የሚታወቀው ነው። አንድ ሜትዮሮይድ ወደ መሬት ከባቢ አየር ከገባ በኋላ በመቃጠል ብርሃን ሲፈጥር የሚሠጠው ስያሜ ነው።

Hewa+ Ad
Ad

ሜትዮራይት (Meteorite)፡ አንድ ሜትዮር ከባቢ አየራችንን አልፎ ሙሉ በሙሉ ሳይቃጠል ምድርን ከነካ ወይም ከወደቀ በኋላ የሚሰጠው ስያሜ ነው። አሁን በጀርመን ህንፃዎች ላይ ያረፉት ስባሪዎች "ሜትዮራይት" ይባላሉ። እነዚህን ማጥናት ስለ ቀደምት የስርዐተ ፀሐይ አመሰራረት ብዙ መረጃ ይሰጠናል።

ነበልባላዊ ተወርዋሪ ኮከቦች (Fireball)፡ እንደ ሜትዮር ወይንም የሰው ሰራሽ ሳተላይት ስባሪ ወደ ከባቢ አየራችን ከገባ በኋላ በሚፈጠረው እፍጋት አማካኝነት በሚፈነዳበት ወቅት የሚፈጠሩ እና ሲነዱ በከፍተኛ ብርሃን የሚታዩ አካላት ናቸው።

ሁሉም "የእሳት ኳስ" የተፈጥሮ ድንጋይ አይደለም (የኢትዮጵያው ክስተት)

ወደ ከባቢ አየራችን በመግባት የእሳት ኳስ (Fireball) የሚፈጥሩት ተፈጥሯዊ ዓለቶች (Asteroids/Meteoroids) ብቻ አይደሉም። ባሳለፍነው ዓመት፣ ጥር 1፣ 2017 ዓ.ም (January 9, 2025) በደቡብ ምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ሰማይ ላይ አስደናቂ ብርሃን ፈጥሮ ያለፈ አካል ታይቶ ነበር።

ባሳለፍነው ዓመት፣ ጥር 1፣ 2017 ዓ.ም (January 9, 2025) በደቡብ ምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ሰማይ የታየው ላይ አስደናቂ ብርሃን

ብዙዎች ክስተቱን የኮከብ መውደቅ አድርገው ቢወስዱትም፣ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ አካል ተፈጥሯዊ ሳይሆን የጠፈር ላይ ስባሪ (Space Debris) ነበር። አካሉ የቻይና የሆነው ሺ ጂያን-19 (ShiJian-19) የተባለ ሳተላይት ቀሪ ክፍል መሆኑ ተረጋግጧል። ሳተላይቱ ተልዕኮውን ጨርሶ ቢመለስም፣ በምህዋር ላይ ሲዞሩ የቆዩት ክፍሎቹ ወደ መሬት ከባቢ አየር ሲገቡ በመቃጠላቸው ምክንያት ያንን አስደናቂ ብርሃን ፈጥረው ነበር።

ስለዚህ፣ በሰማይ ላይ የምናየው እያንዳንዱ የእሳት ኳስ ከተፈጥሮ የመጣ አስትሮይድ ላይሆን ይችላል። የሰው ሰራሽ አካላት ቅሪቶች (Space Debris) ተመሳሳይ ክስተት ይፈጥራሉ።

አደጋው ሲያንዣብብ (የሩሲያው ቼልያቢንስክ ክስተት)

ወደ መሬት የሚደርሱት አብዛኛዎቹ ሜትዮራይቶች ትናንሽ በመሆናቸው የሚያደርሱት ጉዳት እምብዛም ነው። ነገር ግን መጠናቸው ትልቅ የሆኑ የተፈጥሮ አካላት አስቀድመን ሳናያቸው ከገቡ የሚያስከትሉት ጉዳት ከፍተኛ ነው።

ይህ የአውሮጳው ክስተት ወደ ከባቢ አየር ከመግባቱ በፊት በምንም ዓይነት ቴሌስኮፕ አልታየም ነበር። ይህ ሁኔታ እ.ኤ.አ በ2013 በሩሲያ፣ ቼልያቢንስክ (Chelyabinsk) ከተማ ላይ የደረሰውን አስደንጋጭ ክስተት ያስታውሰናል። በወቅቱ ምንም ዓይነት ቅድመ-ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ ወደ ከባቢ አየር የገባው ትልቅ አስትሮይድ፣ መሬት ከመንካቱ በፊት በአየር ላይ ፈነዳ። የፈጠረው ከፍተኛ የድምፅ ሞገድ (Shockwave) በሺዎች የሚቆጠሩ መስኮቶችን አሰባብሮ በርካታ ሰዎችን አቁስሏል።


እነዚህን አደገኛ አካላት አስቀድሞ መለየት ለምን ይከብዳል?

በአውሮጳ የታየው ሜትዮር ወደ መሬት ከመግባቱ በፊት ለምን አልታየም? የመሬት ቅርብ አካላትን (Near Earth Objects - NEOs) አስቀድሞ መለየት ለምን ፈታኝ ሆነ?

መጠናቸው አነስተኛ መሆኑ፡ አብዛኛዎቹ ሜትዮሮይዶች መጠናቸው ጥቂት ሜትሮች በመሆኑ፣ በሰፊው ጠፈር ውስጥ አነስተኛ እና ደብዛዛ ሆነው ይታያሉ። በመሆኑም ኃይለኛ ቴሌስኮፖች እንኳ በቀላሉ ሊያገኟቸው አይችሉም።

የሚመጡበት አቅጣጫ (በተለይ ከፀሐይ በኩል)፡ አንዳንድ ጊዜ አስትሮይዶች ከፀሐይ አቅጣጫ ወደ መሬት ይመጣሉ። በዚህ ጊዜ የፀሐይ ከፍተኛ ብርሃን ቴሌስኮፖቻችንን ስለሚያሳውር፣ አስትሮይዱ ከባቢ አየራችን ውስጥ ገብቶ እስኪቃጠል/እስኪፈነዳ ድረስ ላናየው እንችላለን። ይህ የአውሮጳው ሜትዮርም ወደ መሬት የመጣው ፀሐይ ልትጠልቅ አካባቢ (Dusk)፣ ሰማዩ አሁንም ብሩህ በነበረበት ሰዓት በመሆኑ አስቀድሞ በቴሌስኮፖች ለማየት አዳጋች አድርጎት ነበር። (የቼልያቢንስኩ ሜትዮርም በተመሳሳይ ከፀሐይ አቅጣጫ የመጣ ነበር)።

የመሳሪያዎች ውስንነት እና ስርጭት፡ የራዳር ሲስተሞች እና ቴሌስኮፖች በተወሰኑ የዓለማችን ክፍሎች ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው። ሰፊውን ሰማይ ሙሉ በሙሉ እና በ24 ሰዓት ለመሸፈን አሁንም ቴክኖሎጂው አልደረሰም። እስካሁን ድረስ ወደ መሬት ከገቡት አካላት ውስጥ አስቀድመን ማወቅ የቻልነው 11ዱን ብቻ መሆኑ የክትትሉን አቅም ውስንነት ያሳያል።

መፍትሄው ምንድን ነው?

መጠናቸው ከ20 ሜትር በላይ የሆኑ አደገኛ አካላት አስቀድመው ክትትል የሚደረግባቸው ከሆነ የሚያልፉበትን ምህዋር እና ፍጥነት በመገመት፣ እንደ አስፈላጊነቱ አቅጣጫቸውን በማስቀየር (deflection techniques) መሬትን ከከባድ አደጋ መታደግ ይቻላል።

ለዚህም ነው እንደ አሜሪካው NASA Planetary Defense እና የአውሮጳው ESA ያሉ ተቋማት ክትትላቸውን የሚያጠናክሩት። የአውሮጳ የጠፈር ኤጀንሲ (ESA) በቀን ብርሃን እና ፀሐይ በምትጠልቅበት ሰዓት (Daytime/Dusk) የሚመጡ አካላትን አስቀድሞ ለመለየት የሚያስችለውን የ**"ፍላይ-አይ" (Flyeye asteroid survey telescope)** ፕሮጀክት በማዘጋጀት ላይ ይገኛል። በተጨማሪም በቅርቡ ስራ የጀመረው ቬራ ሩቢን ኦብዘርቫቶሪ (Vera Rubin Observatory) የተባለው ግዙፍ ቴሌስኮፕ ሰማዩን በፍጥነት እና በስፋት የመቃኘት አቅም ስላለው ያልታዩ አስትሮይዶችን የማግኘት ምጣኔን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረው ይገኛል።

የቪራ ሲ. ሩቢን ኦብዘርቫቶሪ

የሕዋ ምርምር ከዕውቀት ባሻገር ራሳችንን ከተፈጥሮ አደጋ ለመጠበቅ ያለውን ወሳኝ ሚና የቅርብ ጊዜዎቹ ክስተቶች በማያሻማ ሁኔታ እያሳዩን ይገኛሉ።

🔗 Sources

Universe Today: "https://www.universetoday.com/articles/sunday-mornings-european-fireball-was-probably-only-a-few-meters-in-diameter" (By Evan Gough) European Space Agency (ESA): ስለ ክስተቱ ዝርዝር ትንታኔ፣ የፕላኔቶች መከላከያ (Planetary Defence) እና የ "Flyeye" ቴሌስኮፕ መረጃዎች የተገኙት ከኤጀንሲው የ Space Safety Programme ወቅታዊ መግለጫዎች ነው። Ethiopian Space Science Society (ESSS): ጥር 2፣ 2017 ዓ.ም (January 10, 2025) የተጻፈው "ጠቅላላ መረጃዎች እና ተደጋግመው የሚነሱ ጥያቄዎች" ።

People Also Like