ወደ ጦማር ይመለሱ

ሥነ-ፈለክ እና አስትሮሎጂ፡ አንድ መስሎ የሚታይ ግን ሰማይ እና ምድር የሆነ ልዩነት

ሥነ-ፈለክ እና አስትሮሎጂ፡ አንድ መስሎ የሚታይ ግን ሰማይ እና ምድር የሆነ ልዩነት

ብዙ ጊዜ "አስትሮኖሚ" እና "አስትሮሎጂ" የሚሉት ቃላት በመመሳሰላቸው ሲምታቱ ይስተዋላል። ሁለቱም ስለ ከዋክብት፣ ስለ ፕላኔቶች እና ስለ ሰማይ አካላት የሚያወሩ ቢሆንም፤ በመካከላቸው ያለው ልዩነት ግን የሳይንስ እና የእምነት (ወይም የውሸት ሳይንስ) ያህል ሰፊ ነው።

ይህ ጽሁፍ፣ የሁለቱን መሰረታዊ ልዩነት እና ታሪካዊ ዳራ በዝርዝር ይዳስሳል።

ሥነ-ፈለክ ምንድን ነው?

ሥነ-ፈለክ የሰው ልጆች በምልከታ፣ በሂሳብ እና በፊዚክስ ህጎች ተጠቅመው ስለ ጽንፈ ዓለም (Universe) የሚያጠኑበት ተፈጥሮአዊ ሳይንስ (Natural Science) ነው።

  • ዓላማው፡ የሰማያዊ አካላትን (ከዋክብት፣ ፕላኔቶች፣ ጋላክሲዎች) አፈጣጠር፣ እንቅስቃሴ እና ባህሪ መረዳት።
  • ዘዴው፡ ቴሌስኮፕ፣ ሳተላይት እና የጠፈር ሮኬቶችን በመጠቀም መረጃ መሰብሰብ እና መተንተን።
  • ጥቅሙ፡ ከጥንት ስልጣኔ ጀምሮ የጊዜ እና የወቅት መለያ በመፍጠር፣ የዝናብ ወቅትና የወንዞችን የመሙያ ጊዜ በመጠቆም ለግብርናው ዘርፍ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። በበረሃና በባህር ላይ ለሚደረጉ ጉዞዎችም እንደ ኮምፓስ አገልግሏል።

አስትሮሎጂ ምንድን ነው?

አስትሮሎጂ (ኮከብ ቆጠራ) የሰማያዊ አካላትን እንቅስቃሴ መሰረት በማድረግ የሰዎችን ዕድል፣ ባህሪ እና የወደፊት ህይወት ለመተንበይ የሚሞከርበት ሃሰተኛ ሳይንስ (Pseudoscience) ነው።

  • መሰረቱ፡ "የፕላኔቶች አቀማመጥ በሰው ልጅ ህይወት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አለው" የሚል ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው እምነት ነው።
  • ለምን ሃሰተኛ ሳይንስ ተባለ? አስትሮሎጂ በምርምር ሊረጋገጥ አይችልም። አንድ ሰው "በዚህ ወር የተወለዱ ሰዎች ቁጡ ናቸው" ቢል፣ ይህንን በላብራቶሪ ወይም በዳታ ማረጋገጥ አይቻልም።
  • ታሪኩ፡ ሰዎች በጊዜ ሂደት ተፈጥሮን መመርመር እና ምክንያታዊ ትንታኔ ለማስቀመጥ በተቸገሩ ጊዜ፣ ለነገሮች ምክንያት ለማስቀመጥ ሲሉ የፈለሰፉት ዘዴ ነው።

ጥንታዊ የኢትዮጵያ አስትሮሎጂያዊ የወራት ስያሜ ፡ ምንጭ አየለ ፡ ጉግል

ታሪካዊ የምርምር ጉዞ፡ ከቻይና እስከ አውሮፓ

ሥነ-ፈለክ በዓለማችን ታላላቅ ስልጣኔዎች ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው።

  • ቻይናውያን: በሶንግ ዳይናሲቲ (Song Dynasty) ጊዜ የነበሩ ተመራማሪዎች የወራቶችን የመጀመሪያ ቀናት እና የጨረቃ ግርዶሽን በከፍተኛ ጥራት ይተነብዩ ነበር። ከ1434 በላይ ከዋክብትን የያዘ ካርታ እና "ፕላኔተሪየም" (ሰው ሰራሽ የከዋክብት አዳራሽ) መገንባት ችለው ነበር።

ሕብረ ከዋክብት በጥንት ቻይናውያን ስነ ፈለክ ምንጭ፡ ውክፔድያ

  • ምዕራባውያን: የቻይናውያን የሥነ-ፈለክ መረጃዎችን በማዋቀር ላይ ሲያተኩር፣ የምዕራቡ አለም ደግሞ ፕላኔቶች እና እንቅስቃሴያቸው ላይ የተመሰረቱ ቲዎሪዎች (Theories) ላይ ያተኮረ ነበር።

የኢትዮጵያ ሚና እና የሥነ-ፈለክ ትስስር

ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ እና በስነ-ዘመን አቆጣጠር (Chronology) የራሷ የሆነ ረጅም ታሪክ አላት።

  • ባሕረ ሃሳብ (Bahire Hasab - Ethiopic Computus): ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት የሚጠቀሙበት ጥንታዊ የስነ-ዘመን ቀመር ነው። ይህ ስርዓት የፀሐይን እና የጨረቃን ዑደት (Solar and Lunar cycles) መሰረት በማድረግ፣ በዓላት የሚውሉበትን ቀን እና ወቅቶችን ለማስላት የሚጠቅም ውስብስብ የሂሳብ እና የከዋክብት ምልከታ ውጤት ነው። ይህም ኢትዮጵያውያን የሰማይ አካላትን ምልከታ ለሳይንሳዊ የቀን አቆጣጠር ይጠቀሙ እንደነበር ማሳያ ነው።
  • የአሁን ጊዜ: ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ከዚህ ጥንታዊ እውቀት በመነሳት ወደ ዘመናዊ የህዋ ሳይንስ እየተሸጋገረች ነው። እንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ (ESSS) ይህንን ዘመናዊ ሳይንስ ለትውልድ ለማድረስ እየሰሩ ይገኛሉ።

እንጦጦ ዖብዘርቫቶሪ

ማጠቃለያ

አስትሮሎጂ፣ የሰው ልጅ ገና ሳይንስ ባልተራቀቀበት ዘመን የፈጠረው እምነት ሲሆን፤ ዓለምን ወደፊት የሚያራምደው፣ ሳተላይቶችን የሚያመጥቀው እና የሰው ልጅን ችግር የሚፈታው ግን ሥነ-ፈለክ (ሳይንስ) ነው።

ስለ ህዋ የበለጠ ማወቅ ይፈልጋሉ? የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲን ይቀላቀሉ! 

🔗 Sources

ጽሁፍ ዝግጅት፡ አሉላ ረዳኢ (ESSS) ተጨማሪ ምንጮች፡ European Space Agency, A History of Astronomy

ሰዎች እነዚህንም ወደዋል