ወደ ጦማር ይመለሱ

የህዋ ምርምርና ሁለንተናዊ ፋይዳው

የህዋ ምርምርና ሁለንተናዊ ፋይዳው

የህዋ ሳይንስ በጠፈር ምርምር ጥናት ውስጥ ጥቅም ላይ የሚዉሉ ሁሉንም መስኮች ያካተተ፣ ከምድር ከባቢ አየር ባሻገር ያሉ የተፈጥሮ ክስተቶችን እና አካላትን የሚያጠና መስክ ነው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃአጋማሽ ላይ የዳበረ እና ስለ ሁለንተና ያለንን እውቀት በፍጥነት እያሳደገ ያለ የምርምር ዘርፍ ነው። የጠፈር ሳይንስ እንደ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ምህንድስና፣ ስነፈለክ ፣ አስትሮፊዚክስ እና አስትሮባዮሎጂ ያሉ የተለያዩ ዘርፎችን ያካትታል። የጠፈር ሳይንስ ጥናት የሚከናወነው በምደር ላይ በመሆን ምልከታ በሚያደርጉ መሳሪያዎችን እንዲሁም ወደ ምድር የላይኛው ከባቢ አየር ወይም ከዚያም በላይ በሚጓዙ እንደ ባሉኖች፣ ሮኬቶች፣ ሳተላይቶች፣ ስፔስ ፕሮቦች፣ ኦርቢተሮች እና ላንደሮችን በመጠቀም ነው። የጠፈር ሳይንስ መስክ ሰፊ እና ብዙ ንዑስ መስኮችን የሚያካትት መስክ ነው። የጠፈር ሳይንስ በውስጡ ከሚይዛቸው ንዑስ መስኮች መካከል አንዳንዶቹ ስነፈለክ ፣ አስትሮፊዚክስ፣ አስትሮባዮሎጂ እና ፕላኔተሪ ሳይንሶች ናቸው።

የጠፈር ሳይንስ ዋና ዋና ዘርፎችን የሚወክል ሥዕላዊ መግለጫ፤ ከሮኬቶችና ከጠፈር ጣቢያዎች እስከ አስትሮፊዚክስ፣ የህዋ ሕክምና እና የሮቦቲክስ አሰሳ ድረስ። በኦፕን ኤአይ (OpenAI) የምስል መፍጠሪያ ቴክኖሎጂ የተዘጋጀ።


የጠፈር ሳይንስ ታሪክ መነሻው የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የፕላኔቶችን እና የከዋክብትን እንቅስቃሴዎች መመልከት እና ማጥናት በጀመሩት እንደ ባቢሎናውያን፣ ግብፃውያን፣ ግሪኮች፣ ህንዶች፣ ቻይናውያን እና በሌሎች ጥንታዊ ስላጣኔዎች ስሆን እነዚህ ስልጣኔዎች በግኝቶቻቸው መሰረት የሂሳብ ሞዴሎችን እና የቀን መቁጠሪያዎችን ፈጥረዋል፡፡ በ16ኛው እና በ17ኛው ክፍለ ዘመን በተካሄደው ሳይንሳዊ አብዮት እንደ ኒኮላስ ኮፐርኒከስ፣ ጋሊልዮ ጋሊሊ፣ ዮሃንስ ኬፕለር እና አይዛክ ኒውተን ያሉ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች የስበት እና የእንቅስቃሴን ህግ እንዲሁም የሄሊዮሴንትሪክ ሞዴልን ወይም ፀሀይ የስረዓተ ፀሐይ ማመዕከላዊ መሆኗን እና ፕኔቶችም በዙሪያዋ እየተሽከረከሩ መሆናቸውን የሚያሳየውን ንድፈ-ሀሳብ በመመስረት የጂኦሴንትሪክ እይታን ወይም ምድር የአጽናፈ ሰማይ ማከዕል እንደሆነች፣ ፀሀይ እና ፕላኔቶችም በዙሪያዋ እየተሽከረከሩ መሆናቸውን የሚያስቀምጠውን ትክክል ያልሆነ ንድፈ ሃሳብ መመከት ችለዋል። በ 20 ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የጠፈር ሳይንስ፤ ሰዎች ከምድር ከባቢ አየር በላይ እንዲሄዱ የሚያስችላቸው አዳዲስ የሳይንስ ንድፈ ሃሳቦች እና የቴክኖሎጂ እድገቶች ማስገኘት ችሏል፡፡ 

ሂፓርከስ ግሪካዊ የሒሳብ ሊቅ እና የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ነበር። ከሥራዎቹ መካከል አንዳቸውም ተርፈው ባይገኙም፣ በ140 ዓ.ም የከዋክብት ካታሎግ ካዘጋጀውና የመጨረሻው ጥንታዊ ግሪካዊ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ከሆነው ከቶለሚ (Ptolemy) ሥራዎች አማካኝነት ስለ ሂፓርከስ ሥራዎች ማወቅ ተችሏል።የምስል ምንጭ፦ ናስታሲክ / ጌቲ ኢሜጅስ

በህዋ ሳይንስ ታሪክ ውስጥ ስለ ጽንፈ ዓለማት ያለንን አመለካከት የቀየሩ በርካታ ጉልህ የለውጥ ጊዜያቶች ነበሩ። እነዚህ ወሳኝ ወቅቶች የሰው ልጅ ፍለጋ ከምድር ወሰንም ባሻገር መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው። እ.ኤ.አ. በ 1957 የሶቪየት ህብረት የመጀመሪያውን አርቲፊሻል የምድር ሳተላይት ስፑትኒክ 1 ን ወደ ህዋ በማምጠቅ ይህንን ተልዕኮ ጀመረች።  እ.ኤ.አ. በ1961 ደግሞ ዩሪ ጋጋሪን ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር ላይ የአንድ ምህዋር ጉዞን አከናወነ፡፡ ይህም ከሰው ልጆች የመጀመሪያው የጠፈር መንገደኛ እንዲሆን አስችሎታል። ቀጥሎም ኒል አርምስትሮንግ እ.ኤ.አ. በ1969 በዩኤስ አፖሎ 11 ተልዕኮ ጨረቃን የረገጠ የመጀመሪያው ሰው ሆነ፡፡ በዚህ ክስተትም የዓለም ህዝቦች ሁሉ ሊማረኩ ችለዋል፡፡ ይህም ክስተት የጠፈር ምርምርን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ አድርጎታል። የአስተሳሰብ አድማሳችንም እጅግ አስፍቶታል። በ1962 የዩናይትድ ስቴትስ የሆነው የማሪንየር 2 ተልእኮ የመጀመሪያውን የሌላ ፕላኔት መረጃ ከቬኑስ በመሆን አስተላለፈ፡፡ የማርስ ፎቶዎች በ1965 በማሪን 4 ተነሱ እንዲሁም በ1976 ቫይኪንግ 1 በማርስ ላይ ያረፈ የመጀመሪያው መንኮራኩር ሆነ። እ.ኤ.አ በ1973 ደግሞ ፓይነር 10 በጋዝ ኃያሏ በጁፒተር ላይ ለመብረር የመጀመሪያዋ የጠፈር መንኮራኩር መሆን ቻለ፡፡ ጁፒተርም የምርምር ትኩረት እንትሆን አደረገ። ካሲኒ-ሃይገንስ በ2004 ባለ ቀለበትቷን አስገራሚ ፕላኔት ሳተርንን ለመዞር የመጀመሪያው የጠፈር መንኮራኩር ሆነች። እ.ኤ.አ. በ 2015 ኒው ሆራይዘን ወደ ፕሉቶ ከደረሰ በኋላ ፣ የዚህችን ሩቅ ድንክ ፕላኔት የመጀመሪያዎቹ ቅርብ ምስሎች ይፋ አደረገ፡፡

እ.ኤ.አ. ጁላይ 20፣ 1969 አሜሪካውያን የጠፈር ተጓዦች ኒል አርምስትሮንግ እና ኤድዊን ባዝ ኦልድሪን ጨረቃ ላይ ያረፉ የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች ለመሆን በቅተዋል። የምስል ምንጭ: ናሳ/ኒውስሜከር/ጌቲ ኢሜጅስ

21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ አዲስ የጠፈር ምርምር ዘመንን አምጥቷል፣ እንደ ስፕስ አኤክስ/ SpaceX እና ብሉ ኦሪገን/ Blue Origin ባሉ ኩባንያዎች እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ሮኬቶች እና የንግድ የጠፈር በረራን ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ እድገቶችን ሊያመጡ ችለዋል። እንደ ኬፕለር እና ቴስ/ TESS ባሉ ተልእኮዎች አማካኝኘት ከፀሀይ ስርዓታችን ባሸገር በሺዎች የሚቆጠሩ ኤክስፖፕላኔቶች ተገኝተዋል። ይህም ስለ ኮስሞስ ያለን ግንዛቤ ማሳደግ ችሏል። በተጨማሪም፣ እንደ ካሪዮሲቲ እና ፐርሲቨረንስ ያሉ ተልእኮዎች በማርስ ላይ የህይወት መረጃዎችን ለመፈለግ የቀይዋን ፕላኔት አሰሳን ይበልጥ አጠናክረዋል። እነዚህ ወሳኝ ክንውኖች ባለፉት ዘመናት እና ባሁኑ ጊዜም የሰዉ ልጆችን የማወቅ ጉጉት ያቀጣጠሉ እናም ያልታወቀን ለማወቅ መነሳሳትን የፈጠሩ ክንውኖች ናቸው። 

የኤስ.ኢ.ኤስ-10 (SES-10) የመገናኛ ሳተላይትን ወደ ምህዋር ካመጠቀ በኋላ ዳግም ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው የSpaceX Falcon 9 ሮኬት የመጀመሪያው ክፍል በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ በሚገኘው የSpaceX ድሮን ሽፕ' (drone ship) ላይ ለማረፍ እየወረደ የሚያሳይ ምስል። የምስል ምንጭ፦ ስፔስ ኤክስ

የተለያዩ ፈጠራዎችም የጠፈር ምርምር ወጤቶች ናቸው። በተለይ እንደ የሳተላይት ቴክኖሎጂ፣ ጂፒኤስ እና የመገናኛ አውታሮች ባሉ የቴክኖሎጂ መስኮች እድገደት ላይ ቁልፍ ሚናን ይጫወታል፡፡ በዕለት ተዕለት ህይወታችን እንደ ቀላል ነገር የምንወስዳቸው አብዛኛዎቹ ቴክኖሎጂዎች እንደ የፀሐይ ፓነሎች ፣ የ LED መብራቶች ፣ ሰው ሰራሽ እግሮች ፣ የውሃ ማጣሪያዎች እና የመሳሰሉ የቴክሊፈጠሩ የቻሉት ወይም ደግሞ ጉልህ የሆኑ ማሻሻያዎችን ያገኙት በህዋ ተልዕኮዎች አማካኝነት ነው።ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እድገት ባሻገር የጠፈር ምርምር መነሳሳትን በመፍጠር ረገድ አቻ አይገኝለትም፡፡ በሁሉም የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ወይም በተለያዩ የስራ መስኮችኙ ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ስለጠፈር የማወቅ ፍላጎት አላቸው፡፡ ይህ ፍላጎት እና ተነሳሽነትም በተወሰኑ ነገሮችብቻ የተገደበ አይደለም ከአጽናፈ ዓለም ጋር ያለንን ቁረኝት የሚያጎሉ አዳዲስ የሥነ ጽሑፍ፣ የሙዚቃ፣ የኪነጥበብ እና የመገናኛ ብዙኃን ሥራዎች እንዲፈጠሩ አድርጎአል፡፡ 

በተጨማሪም የጠፈር ምርምር ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ያጎለብታል፡፡ የተለያዩ አገሮችን እና ባህሎችን አንድ ለማድረግ እና አንድ ዓላማን ለማሳካት፣ ሰላማዊ ትብብርንም ለማስፋፋት ጉለህ ሚና ይጫወታል፡፡ ከ15 አገሮች የተውጣጡ አምስት የጠፈር ኤጀንሲዎችን ተስትፎ ያለበት እንደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ/ ኢንተርናሽናል ስፔስ ስቴሸን ያሉ ግዙፍ ፕጀክቶች በህዋ ምርምር ላይ ላለው ዓለም አቀፋዊ ትብብር ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር የጠፈር ምርምር ፕላኔታችንን ለመከታተል እና ለመጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። ሳተላይቶችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን በመጠቀም የአካባቢ ለውጦችን መመልከት እና ምላሽ መስጠት እንድንችል አድርጎናል፡፡ የጠፈር ሳይንስ እንደ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የእሳተ ገሞራ እና የሰደድ እሳት ላሉ ክስተቶች የቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠትየተፈጥሮ አደጋዎችን ተፅእኖ በመቀነስ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። 

ባለፉት 20 ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ፤ ካናዳ፣ 16ቱ የአውሮፓ ጠፈር ኤጀንሲ (ESA) አባል አገራት፣ ጃፓን እና ሩሲያ ዓለም አቀፉን የጠፈር ጣቢያ (ISS) በማብረርና በማንቀሳቀስ ረገድ በታላቅ ስኬት በጋራ ሠርተዋል። ምንጭ: ናራይስ ዩኒቨርሲቲስ ቤከር ኢንስቲትዩት ፎር ፐብሊክ ፖሊሲ

በአጠቃላይ የህዋ ምርምር ሳይንሳዊ እውቀታችንን የሚያበለጽግ ብቻ ሳይሆን ስለ አጽናፈ ሰማይ እና ስለራሳችን ያለንን ግንዛቤ የሚያሳድግ እንዲሁም ሰለ ሁለንተና ላሉን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በጋራ ለምናደርገው ጥረት ማሳያ ሆኖ ይቆማል። በውስጡም የሚይዛቸው ዘርፎች የዘመናችን ታላላቅ የጥናት መስኮች ከመሆናቸውም በላይ፣ ስለ ሁለንተና ጥልቅ ግንዛቤን በመስጠት፣ ፈጠራን በተለያዩ ዘርፎች በማጎልበት፣ የሰው ልጆችን ህይወት ለማሻሻል የሚያስፈልጉንን መሳሪያዎችን በማቅረብ እንዲሁም ሃገራትን በትብብር መንፈስ አንድ በማድረግ ላይ ናቸው።


ሰዎች እነዚህንም ወደዋል