በየአመቱ ምድር የተፈጥሮ የቀን ብርሃን ሰዓታት ለውጥ ያጋጥማታል። አንዳንዶቹ ቀናት ረጅም የፀሐይ ብርሃን የሚታይባቸው ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ ረጅም ሌሊት ያላቸው አጭር ቀናት ናቸው። ሶልስቲስ (Solstice) በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከሰት ሲሆን ፀሐይ ከምድር ወገብ በጣም ርቃ (ወደ ሰሜን ወይም ደቡብ) የምትገኝበት ወቅት ነው። ይህም የቀንና የሌሊት ልዩነት ከፍተኛ እንዲሆን ያደርጋል። ኢኳኖክስ (Equinox) "እኩል ሌሊት" ማለት ሲሆን ፀሐይ በቀጥታ በምድር ወገብ ላይ ስለምትሆን በመላው ዓለም የቀንና የሌሊት ርዝማኔ እኩል (12 ሰዓት) ይሆናል።

ምድር በፀሐይ ዙሪያ የምታደርገውን ዑደት፣ የታህሳስ እና የሰኔ ሶልስቲስን እንዲሁም ሁለቱ ኢኳኖክሶች ስእላዊ መግለጫ | ምስል ምንጭ፦ በቢቢሲ ስካይ አት ናይት ማጋዚን
የአመቱ አጭር ቀን በዚህ ዑደት ውስጥ ቁልፍ ወቅት ሲሆን የታህሳስ ሶልስቲስ (December Solstice) ተብሎ ይታወቃል። ሶልስቲስ የሚከሰተው ምድር በፀሐይ ዙሪያ በሚኖራት ምህዋር ላይ በ23.5 ዲግሪ ዘንበል ብላ ስለምትጓዝ ነው። ይህ የምድር ዝንባሌ እንደየሀገራቱ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተለያየ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ለምድር ወገብ ቅርብ ስትሆን (በ3° እና 15° ሰሜን ላቲቲዩድ መካከል) ትገኛለች። በዚህ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ምክንያት፣ ሀገሪቱ ከሰሜን ወይም ከደቡብ የዓለም ክፍሎች በተለየ ከፍተኛ የቀን ብርሃን ለውጥ አታይም።

የአዲስ አበባ ምሽት | የምስል ምንጭ፦ Local Government Research Initiative
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያም ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ዑደት ውጭ አይደለችም። በሌሎች የዓለም ክፍሎች እንደሚታየው ግዙፍ ለውጥ ባይሆንም፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይም የፀሐይ መውጫ እና መግቢያ ሰዓታት ላይ መጠነኛ የሆነ የደቂቃዎች ልዩነት ይታያል።እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025፣ የታህሳስ ሶልስቲስ (የክረምት ሶልስቲስ) እሁድ ታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም (December 21, 2025) ከሰዓት በኋላ በ12፡03 (18:03) ላይ ተከስቷል ። በኢትዮጵያ ይህ ቀን የሚከተሉት ልዩ ባህሪያት አሉት፡-
- ይህ ቀን በሰኔ ወር ከሚኖረው ረጅሙ ቀን (June Solstice) ጋር ሲነጻጸር በ1 ሰዓት ከ3 ደቂቃ ያጥራል።
- ፀሐይ በቀትር ሰዓት በሰማይ ላይ ዝቅተኛውን መስመር ትከተላለች።
- ከምድር ወገብ በስተሰሜን በሚገኙ አብዛኞቹ አካባቢዎች (ኢትዮጵያን ጨምሮ)፣ ይህ የአመቱ አጭሩ ቀን ነው።

ሰንጠረዥ፦ በአዲስ አበባ የዓመቱ ወቅታዊ የቀን ብርሃን ለውጦች | የመረጃ ምንጭ፦ ታይም ኤንድ ዴት (Time and Date) - አዲስ አበባ
የታህሳስ ሶልስቲስ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ከፍተኛ ለውጥ ቢያመጣም፣ በኢትዮጵያ ግን ለውጡ መጠነኛ ሆኖ ያልፋል። ያም ሆኖ ግን ይህ ክስተት ከፀሐይ ጋር ያለንን ተለዋዋጭ ግንኙነት የሚያሳይ ጠቃሚ የስነፈለክ መለኪያ ነው።